አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤ እነሆ፤ ጻድቁና አዳኙ ንጉሥሽ፣ ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣ በአህያ ግልገል፣ በውርንጫዪቱ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል። ሠረገሎችን ከኤፍሬም፣ የጦር ፈረሶችን ከኢየሩሳሌም እወስዳለሁ፤ የጦርነቱም ቀስት ይሰበራል፤ ሰላምን ለአሕዛብ ያውጃል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፣ ከወንዙም እስከ ምድር ዳር ድረስ ይዘረጋል። ለአንቺ ደግሞ፣ ከአንቺ ጋራ ከገባሁት የደም ቃል ኪዳን የተነሣ፣ እስረኞችሽን ውሃ ከሌለበት ጕድጓድ ነጻ እለቅቃቸዋለሁ። እናንተ በተስፋ የምትኖሩ እስረኞች፤ ወደ ምሽጎቻችሁ ተመለሱ፤ አሁንም ቢሆን ሁለት ዕጥፍ አድርጌ እንደምመልስላችሁ እናገራለሁ። ቀስቴን እንደ ገተርሁ፣ ይሁዳን እገትረዋለሁ፤ ኤፍሬምንም ፍላጻ አደርገዋለሁ። ጽዮን ሆይ፤ ልጆችሽን አስነሣለሁ፤ ግሪክ ሆይ፤ በአንቺ ልጆች ላይ ይነሣሉ፤ እንደ ተዋጊ ሰይፍም አደርግሻለሁ። እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ይገለጣል፤ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤ ጌታ እግዚአብሔር መለከት ይነፋል፤ በደቡብም ዐውሎ ንፋስ ውስጥ ይጓዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ይከልላቸዋል፤ ጠላቶቻቸውን ይደመስሳሉ፤ በድንጋይ ወንጭፍም ያሸንፋሉ፤ ይጠጣሉ፤ በወይን ጠጅ እንደ ሰከረ ሰው ይጮኻሉ፤ የመሠዊያውን ማእዘኖች ለመርጨት፣ እንደ ተዘጋጀ ዕቃ፣ እነርሱም እንደዚሁ ተሞልተዋል። ሕዝቡን የራሱ መንጋ አድርጎ በዚያ ቀን አምላካቸው እግዚአብሔር ያድናቸዋል። በአክሊል ላይ እንዳለ ዕንቍ፣ በገዛ ምድሩ ላይ ያብለጨልጫሉ። እንዴት ውብና አስደናቂ ይሆናሉ፤ እህል ጕልማሶችን፣ አዲስ የወይን ጠጅም ቈነጃጅትን ያሳምራል።
ዘካርያስ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘካርያስ 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘካርያስ 9:9-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች