ስለ እስራኤል የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። ሰማያትን የዘረጋ፣ ምድርን የመሠረተ፣ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የሚያንገደግድ ጽዋ አደርጋታለሁ፤ ይሁዳም እንደ ኢየሩሳሌም ሁሉ ትከበባለች። የምድር አሕዛብ ሁሉ በርሷ ላይ በሚሰበሰቡበት በዚያ ቀን፣ ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ የማይነቃነቅ ዐለት አደርጋታለሁ፤ ለማነቃነቅ የሚሞክሩ ሁሉ ራሳቸውን ይጐዳሉ። በዚያ ቀን እያንዳንዱን ፈረስ በድንጋጤ፣ የተቀመጡባቸውንም ሰዎች በእብደት እመታለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “የይሁዳን ቤት በዐይኔ እጠብቃለሁ፤ ነገር ግን የአሕዛብን ፈረሶች ሁሉ አሳውራለሁ። የይሁዳ መሪዎች በልባቸው፣ ‘የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ብርቱ ናቸው፤ አምላካቸው የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነውና’ ይላሉ። “በዚያ ቀን የይሁዳን መሪዎች በዕንጨት ክምር ውስጥ እንዳለ የእሳት ምድጃ፣ በነዶም መካከል እንዳለ የፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፤ በግራና በቀኝ ዙሪያውን ያሉትን ሕዝቦች ይበላሉ፤ ኢየሩሳሌም ግን ከስፍራዋ ንቅንቅ አትልም። “የዳዊት ቤትና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ክብር ከይሁዳ ክብር እንዳይበልጥ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የይሁዳን መኖሪያዎች ያድናል። ከመካከላቸው እጅግ ደካማ የሆነው እንደ ዳዊት፣ የዳዊት ቤትም ፊት ፊታቸው እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ፣ እንደ አምላክ ይሆንላቸው ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እግዚአብሔር ይከልላቸዋል። በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን በወጓት አሕዛብ ሁሉ ላይ እወጣለሁ። “በዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የርኅራኄና የልመና መንፈስ አፈስሳለሁ፤ ወደ ወጉኝ ወደ እኔም ይመለከታሉ፤ እነርሱም ለአንድያ ልጅ እንደሚለቀስ ያለቅሱለታል፤ ለበኵር ልጅ ምርር ተብሎ እንደሚለቀስም አምርረው ያለቅሱለታል።” በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ ለሐዳድሪሞን እንደ ተለቀሰ ሁሉ በኢየሩሳሌም የሚለቀሰውም እንደዚሁ ታላቅ ልቅሶ ይሆናል። ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ የየነገዱ ወንዶች ለየራሳቸው ያለቅሳሉ፤ ሚስቶቻቸውም ለየራሳቸው ያለቅሳሉ፤ በዚህም ዐይነት የዳዊት ቤት ነገድ ወንዶች ከነሚስቶቻቸው፣ የናታን ቤት ነገድ ወንዶች ከነሚስቶቻቸው፣ የሌዊ ቤት ነገድ ወንዶች ከነሚስቶቻቸው፣ የሰሜኢ ቤት ነገድ ወንዶች ከነሚስቶቻቸው፣ የቀሩትም ነገዶች ወንዶች ሁሉ ከነሚስቶቻቸው ያለቅሳሉ።
ዘካርያስ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘካርያስ 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘካርያስ 12:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች