ሩት 2:17-23

ሩት 2:17-23 NASV

ስለዚህ ሩት እስኪመሽ ድረስ ከአዝመራው ላይ ቃረመች፤ ከዚያም የሰበሰበችውን ገብስ ወቃች፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያም ያህል ሆነ። ያንም ይዛ ወደ ከተማ ሄደች፤ ዐማቷም የሰበሰበችው ምን ያህል እንደ ሆነም አየች፤ እንዲሁም ሩት የሚበቃትን ያህል ከበላች በኋላ አስተርፋ የነበረውን አውጥታ ለርሷ ሰጠቻት። ዐማቷም፣ “ዛሬ የቃረምሽው ከየት ነው? የትስ ቦታ ስትሠሪ ዋልሽ? መልካም ነገር ያደረገልሽ ሰው የተባረከ ይሁን” አለቻት። ከዚያም ሩት ስትሠራ ስለ ዋለችበት ስፍራ ባለቤት ለዐማቷ ነገረቻት፤ እርሷም፣ “ዛሬ ስቃርም የዋልሁበት አዝመራ ባለቤት፣ ስሙ ቦዔዝ ይባላል” አለቻት። ኑኃሚንም ምራቷን፣ “በጎነቱን ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ማድረጉን ያልተወ እግዚአብሔር ይባርከው” አለቻት፤ ቀጥላም፣ “ሰውየው እኮ የሥጋ ዘመዳችን ነው፤ የመቤዠት ግዴታ ካለባቸው ዘመዶቻችን አንዱ እርሱ ነው” አለቻት። ከዚያም ሞዓባዊቷ ሩት፣ “ደግሞም፣ ‘እህሌን ሁሉ ዐጭደው እስኪጨርሱ ድረስ ከሠራተኞቼ አትለዪ!’ ብሎኛል” አለቻት። ኑኃሚንም ምራቷን ሩትን፣ “የእኔ ልጅ፤ እንዲህ ካልሽማ ከሴት ሠራተኞቹ ጋራ ዐብሮ መሄድ ይሻልሻል፤ ወደ ሌላ ሰው አዝመራ ብትሄጂ ጕዳት ሊያገኝሽ ይችላልና” አለቻት። ስለዚህ የገብሱና የስንዴው አዝመራ ተሰብስቦ እስኪያበቃ ድረስ፣ ሩት የቦዔዝን ሴቶች ሠራተኞች ተጠግታ ቃረመች፤ ከዐማቷም ጋራ ኖረች።