ሮሜ 9:9-21

ሮሜ 9:9-21 NASV

“ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ተብሎ ተስፋው ተሰጥቷልና። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የርብቃ ልጆች አንድ አባት አላቸው፤ እርሱም አባታችን ይሥሐቅ ነው። መንትዮቹ ገና ሳይወለዱ፣ ወይም በጎም ሆነ ክፉ ሳያደርጉ፣ የእግዚአብሔር ሐሳብ በምርጫ ይጸና ዘንድ፣ በሥራ ሳይሆን ከጠሪው በመሆኑ፣ “ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” ተብሎ ተነገራት። ይህም፣ “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዐመፃ አለን? ፈጽሞ! ለሙሴ፣ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ” ይላልና። እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው። መጽሐፍ ፈርዖንን፣ “ኀይሌ በአንተ እንዲታይ፣ ስሜም በምድር ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሣሁህ” ይላልና። ስለዚህ እግዚአብሔር ሊምረው ለሚወድደው ምሕረት ያደርግለታል፤ ልቡ እንዲደነድን የፈለገውንም ያደነድነዋል። ከእናንተ አንዱ፣ “ታዲያ እንደዚህ ከሆነ እግዚአብሔር እስከ አሁን ለምን ይወቅሠናል? ምክንያቱም ፈቃዱን ሊቋቋም የሚችል ማን አለ?” ይለኝ ይሆናል። ነገር ግን ለእግዚአብሔር መልስ የምትሰጥ አንተ ማን ነህ? “ሥራ ሠሪውን፣ ‘ለምን እንዲህ ሠራኸኝ?’ ይለዋልን?” ሸክላ ሠሪ፣ ከሚሠራው ጭቃ፣ አንዳንዱን ሸክላ ለከበረ፣ ሌሎቹን ደግሞ ለተራ አገልግሎት የማድረግ መብት የለውምን?