ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፤ ምክንያቱም የሕይወት መንፈስ ሕግ በክርስቶስ ኢየሱስ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቷችኋል። ሕግ ከሥጋ ባሕርይ የተነሣ ደክሞ ሊፈጽም ያልቻለውን፣ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሰው አምሳል፣ የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆን በመላክ ፈጸመው፤ በዚህም ኀጢአትን በሥጋ ኰነነ፤ ይኸውም በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ በምንመላለስ በእኛ፣ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ነው። እንደ ሥጋ የሚኖሩ ሐሳባቸውን በሥጋ ፍላጎት ላይ ያሳርፋሉ፤ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን ሐሳባቸውን በመንፈስ ፍላጎት ላይ ያደርጋሉ። የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ለኀጢአት የተገዛ አእምሮ ከእግዚአብሔር ጋራ ጠበኛ ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛም፤ መገዛትም አይችልም። በሥጋ የሚመሩትም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይችሉም። እናንተ ግን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ፣ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ናችሁ። ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፣ እርሱ የክርስቶስ አይደለም። ነገር ግን ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ፣ ሰውነታችሁ ከኀጢአት የተነሣ የሞተ ቢሆንም፣ መንፈሳችሁ ከጽድቅ የተነሣ ሕያው ነው። ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ግዴታ አለብን፤ ይሁን እንጂ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም። እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና፤ ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “ አባ ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና፤ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋራ ሆኖ ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋራ ዐብረን ወራሾች ነን።
ሮሜ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ ሮሜ 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሮሜ 8:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች