ሮሜ 3:19-26

ሮሜ 3:19-26 NASV

እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደ ሆነ፣ እናውቃለን፤ ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም ሥጋ ለባሽ በርሱ ፊት ሊጸድቅ አይችልም፤ ይልቁንም በሕግ አማካይነት ኀጢአትን እንገነዘባለን። አሁን ግን ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧል። ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው። ልዩነት የለም፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል፤ በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተሰረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ በአሁኑ ዘመን እግዚአብሔር ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን ለማሳየት ነው።