ሮሜ 3:1-31

ሮሜ 3:1-31 NASV

ታዲያ አይሁዳዊ መሆን ጥቅሙ ምንድን ነው? መገረዝስ ምን ፋይዳ አለው? በየትኛውም መንገድ ጥቅሙ ብዙ ነው፤ ከሁሉ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃል በዐደራ የተሰጠው ለእነርሱ ነው። አንዳንዶች እምነት ባይኖራቸውስ? የእነርሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ ያሳጣዋልን? ከቶ አይሆንም! ይልቅስ እግዚአብሔር እውነተኛ፣ ሰው ሁሉ ግን ሐሰተኛ ይሁን፤ “በቃልህ ትጸድቅ፣ በፍርድም ፊት ረቺ ትሆን ዘንድ” ተብሎ ተጽፏልና። የእኛ ዐመፃ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አጕልቶ የሚያሳይ ከሆነ፣ ምን ማለት እንችላለን? እንደ ሰው ለመከራከር ያህል እግዚአብሔር በእኛ ላይ ቍጣውን በማምጣቱ ዐመፀኛ ነውን? እንደ ሰው ሲታሰብ ማለቴ ነው። ከቶ አይሆንም! እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ እግዚአብሔር በዓለም ላይ እንዴት ሊፈርድ ይችላል? “የእኔ ውሸተኛ መሆን የእግዚአብሔርን እውነተኛነት የሚያጐላ፣ ክብሩንም የሚጨምርለት ከሆነ፣ ኀጢአተኛ ተብዬ እስካሁን እንዴት ይፈረድብኛል?” በማለት ሊከራከር የሚችል ሰው ይኖር ይሆናል። ይህማ “በጎ እንዲመጣ ክፉ እንሥራ” ይላሉ በማለት አንዳንዶች እንደሚያስወሩብን ነው፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፍርድ ትክክለኛ ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? እኛ ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ፣ ሁሉም ከኀጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከስሰናቸዋል። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ጻድቅ ማንም የለም፤ አንድ እንኳ፤ አስተዋይ የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚሻ አንድም የለም። ሁሉም ተሳስተዋል፤ በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ መልካም የሚያደርግ የለም፤ አንድ እንኳ።” “ጕረሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ።” “በከንፈሮቻቸው የእባብ መርዝ አለ።” “አፋቸው ርግማንና ምሬት ሞልቶበታል።” “እግሮቻቸው ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ በመንገዶቻቸው ጥፋትና ጕስቍልና ይገኛሉ፤ የሰላምንም መንገድ አያውቁም።” “በዐይናቸው ፊት ፈሪሀ እግዚአብሔር የለም።” እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደ ሆነ፣ እናውቃለን፤ ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም ሥጋ ለባሽ በርሱ ፊት ሊጸድቅ አይችልም፤ ይልቁንም በሕግ አማካይነት ኀጢአትን እንገነዘባለን። አሁን ግን ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧል። ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው። ልዩነት የለም፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል፤ በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተሰረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ በአሁኑ ዘመን እግዚአብሔር ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን ለማሳየት ነው። ታዲያ ትምክሕት ወዴት ነው? እርሱማ ቀርቷል። በየትኛው ሕግ? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፤ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ማንም ሰው ሕግን በመፈጸም ሳይሆን፣ በእምነት እንደሚጸድቅ እናረጋግጣለን። እግዚአብሔር የአይሁድ አምላክ ብቻ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን፤ የአሕዛብም አምላክ ነው፤ የተገረዘውን በእምነት፣ ያልተገረዘውንም በዚያው እምነት የሚያጸድቅ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና። ታዲያ እንዲህ ከሆነ ከእምነት የተነሣ ሕግን ዋጋ የሌለው እናደርግ ይሆን? ፈጽሞ አይደረግም፤ ሕጉን እናጸናለን እንጂ።