ሕግ ሳይኖራቸው ኀጢአት የሠሩ ሁሉ ያለ ሕግ ይጠፋሉ፤ ሕግ እያላቸው ኀጢአት የሠሩ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሚባሉት ለሕጉ የሚታዘዙ እንጂ፣ ሕጉን የሚሰሙ አይደሉም። ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸውም እነርሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው። ኅሊናቸው ስለሚመሰክር፣ ሐሳባቸው ስለሚከስሳቸው፣ ደግሞም ስለሚከላከልላቸው የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ። ይህም በወንጌል እንደማስተምረው እግዚአብሔር በሰው ልብ የተሰወረውን በክርስቶስ በኩል በሚፈርድበት ዕለት ግልጽ ይሆናል። አንተ ይሁዲ ነኝ ካልህ፣ በሕግ የምትተማመንና ከእግዚአብሔር ጋራ ባለህ ግንኙነት የምትኵራራ፣ በሕግ በመመራትህም ፈቃዱን ዐውቀህ ፍጹም የሆነውን ለይተህ ከያዝህ፣ ለዕውሮች መሪ፣ በጨለማ ላሉትም ብርሃን መሆንህን ርግጠኛ ከሆንህ፣ በሕጉም ካገኘኸው ዕውቀትና እውነት የተነሣ አላዋቂ ለሆኑት መካሪ፣ ለሕፃናት አስተማሪ ከሆንህ፣ እንግዲህ አንተ ሌሎችን የምታስተምር፣ ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ፣ ትሰርቃለህን? አንተ ሰዎች ማመንዘር የለባቸውም የምትል፣ ታመነዝራለህን? አንተ ጣዖትን የምትጸየፍ፣ ቤተ መቅደስን ትመዘብራለህን? አንተ በሕግ የምትመካ፣ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን? ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ ይሰደባል” ተብሎ እንደ ተጻፈው መሆኑ ነው። ሕግን የምትፈጽም ከሆነ ግዝረት ዋጋ አለው፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን እንዳልተገረዝህ ሆነሃል። ያልተገረዙት ሕጉ የሚያዝዘውን የሚፈጽሙ ከሆነ፣ እንደ ተገረዙ አይቈጠሩምን? አንተ የተጻፈ ሕግ፣ ግዝረትም ቢኖርህ፣ ሕግ ተላላፊ በመሆንህ፣ በሥጋ ያልተገረዘው ለሕግ በመታዘዙ ይፈርድብሃል። አንድ ሰው ለይምሰል በውጫዊው ብቻ ይሁዲ ልሁን ቢል ይሁዲ አይሆንም፤ እውነተኛ ግዝረትም ውጫዊና ሥጋዊ ሥርዐት አይደለም። ዳሩ ግን አንድ ሰው ይሁዲ የሚሆነው በውስጣዊ ማንነቱ ይሁዲ ሆኖ ሲገኝ ነው። ግዝረትም ግዝረት የሚሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ በመንፈስ የልብ ግዝረት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ሰው ምስጋናው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
ሮሜ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ሮሜ 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሮሜ 2:12-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች