ሌላው በጣለው መሠረት ላይ እንዳልገነባ ብዬ፣ ክርስቶስ ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን መስበክ የዘወትር ምኞቴ ነበር። ይልቁንም፣ “ስለ እርሱ ያልተነገራቸው ያያሉ፤ ያልሰሙትም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህም ምክንያት ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልሁ። አሁን ግን በእነዚህ አካባቢዎች የምሠራው ስለሌለ፣ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ እናንተን ለማየት እናፍቅም ስለ ነበር፣ ይህን ዕቅድ ወደ እስጳንያ በምሄድበት ጊዜ ልፈጽመው ዐስባለሁ። በማልፍበትም ጊዜ ልጐበኛችሁና ከእናንተ ጋራ ለጥቂት ጊዜ ቈይቼ ናፍቆቴን ከተወጣሁ በኋላ በጕዞዬ እንደምትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን ግን በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ነኝ። ምክንያቱም መቄዶንያና አካይያ፣ በኢየሩሳሌም ካሉት ቅዱሳን መካከል የሚገኙትን ድኾች ለመርዳት ተነሣሥተዋልና። ርዳታ ለማድረግ ወድደዋል፤ በርግጥም ባለዕዳዎቻቸው ናቸው። አሕዛብ የአይሁድ መንፈሳዊ በረከት ተካፋዮች ከሆኑ፣ ያገኙትን ምድራዊ በረከት ከአይሁድ ጋራ ይካፈሉ ዘንድ የእነርሱ ባለዕዳዎች ናቸው። ስለዚህ ሥራውን ከጨረስሁና ይህን ፍሬ መቀበላቸውን ካረጋገጥሁ በኋላ ወደ እስጳንያ እሄዳለሁ፤ እግረ መንገዴንም እናንተን አያለሁ። ወደ እናንተም ስመጣ፣ በክርስቶስ በረከት ሙላት እንደምመጣ ዐውቃለሁ። ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የተጋድሎዬ አጋር እንድትሆኑ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ። በይሁዳ ካሉት ከማያምኑት እጅ እንድድንና በኢየሩሳሌም ያለው አገልግሎቴም በዚያ ባሉት ቅዱሳን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጸልዩልኝ፤ ይኸውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ በደስታ እንድመጣና ከእናንተም ጋራ እንድታደስ ነው። የሰላም አምላክ ከሁላችሁ ጋራ ይሁን። አሜን።
ሮሜ 15 ያንብቡ
ያዳምጡ ሮሜ 15
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሮሜ 15:20-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች