ሮሜ 15:1-20

ሮሜ 15:1-20 NASV

እኛ ብርቱዎች የሆንን፣ የደካሞችን ጕድለት መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን ለማነጽ፣ እርሱንም ለመጥቀም ደስ የሚያሠኘውን ነገር ማድረግ ይገባናል። ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሠኘምና፤ ነገር ግን፣ “አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ደረሰብኝ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ሆነበት። በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና። ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ አንድ ሐሳብ ይስጣችሁ፤ ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንደ ተቀበላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ለእግዚአብሔር እውነት ሲል ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ እንደ ሆነ እነግራችኋለሁና፤ እንዲሁም አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ።” ደግሞም፣ “አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋራ ደስ ይበላችሁ” ይላል። እንደ ገናም፣ “አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑት፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወድሱት” ይላል። ኢሳይያስም እንዲሁ፣ “በሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚነግሠው፣ የእሴይ ሥር ይመጣል፤ በርሱም ሕዝቦች ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል። በርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስስላችሁ ነው። ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነት የተሞላችሁ፣ በዕውቀትም ሁሉ የተሞላችሁና አንዱ ሌላውን ለመምከር ችሎታ ያላችሁ መሆናችሁን እኔ ራሴ ርግጠኛ ሆኛለሁ። እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት፣ እንደ ገና አሳስባችሁ ዘንድ በአንዳንድ ጕዳዮች ላይ በድፍረት የጻፍሁላችሁ፣ በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርን በማገልገሌ በክርስቶስ ኢየሱስ እመካለሁ። በተናገርሁትና ባደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር መንፈስ ኀይል፣ በምልክቶችና በታምራት ነበር። በዚህም ሁኔታ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ። ሌላው በጣለው መሠረት ላይ እንዳልገነባ ብዬ፣ ክርስቶስ ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን መስበክ የዘወትር ምኞቴ ነበር።