ሮሜ 14:10-18
ሮሜ 14:10-18 NASV
ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ለምንስ ወንድምህን ትንቃለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “ ‘እኔ ሕያው ነኝና’ ይላል ጌታ፤ ‘ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር ይመሰክራል።’ ” ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። ስለዚህ እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ በዚህ ፈንታ ግን በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቍርጥ ሐሳብ አድርግ። በጌታ በኢየሱስ ሆኜ በራሱ ንጹሕ ያልሆነ ምንም ምግብ እንደሌለ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን አንድ ሰው አንድን ነገር ንጹሕ እንዳልሆነ የሚቈጥር ከሆነ፣ ያ ነገር ለርሱ ንጹሕ አይደለም። ወንድምህ በምትበላው ምግብ የሚያዝን ከሆነ፣ በፍቅር አልተመላለስህም፤ ክርስቶስ የሞተለትን ወንድምህን በመብልህ አታጥፋው። መልካም ነው ብለህ የምታስበው ነገር ክፉ ተብሎ እንዲነቀፍ አታድርግ። የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ሐሤት ነው እንጂ፣ የመብልና የመጠጥ ጕዳይ አይደለም፤ በዚህ ሁኔታ ክርስቶስን የሚያገለግል እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፤ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው።

