ሮሜ 10:1-21

ሮሜ 10:1-21 NASV

ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እስራኤላውያን የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው። ለእግዚአብሔር ቀናተኞች እንደ ሆኑ ስለ እነርሱ መመስከር እችላለሁና፤ ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም። ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ጽድቅ ስላላወቁና የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለ ፈለጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። ለሚያምን ሁሉ ጽድቅ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ሙሴ በሕግ በኩል የሆነውን ጽድቅ ሲገልጽ፣ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ሕያው ይሆናል” ይላል። ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘በልብህ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?’ አትበል”፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ “ወይም ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል”፤ ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው፤” የምንሰብከውም የእምነት ቃል ይህ ነው፤ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና። መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ? ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኗል?” ብሏልና። እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው። ነገር ግን አልሰሙ ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በርግጥ ሰምተዋል፤ “ድምፃቸው በምድር ሁሉ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ተሰማ።” ደግሜም እጠይቃለሁ፤ እስራኤል አላስተዋሉ ይሆን? በቅድሚያ ሙሴ እንዲህ ይላል፤ “ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤ ማስተዋል በሌለው ሕዝብም አስቈጣቸዋለሁ” ኢሳይያስም በድፍረት፣ “ላልፈለጉኝ ተገኘሁላቸው፤ ላልጠየቁኝም ራሴን ገለጥሁላቸው” ይላል። ስለ እስራኤል ግን፣ “ወደማይታዘዝና ዕሺ ወደማይል ሕዝብ፣ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ” ይላል።