ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ፣ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤ ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ተሰጠ። ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ፣ በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን። እናንተም ራሳችሁ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከተጠሩት መካከል ናችሁ። በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ በሮም ላላችሁ ሁሉ፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ከሁሉ አስቀድሜ፣ እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። ሁልጊዜ ምን ያህል እንደማስባችሁ፣ የልጁን ወንጌል በመስበክ በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ በጸሎቴ ሁልጊዜ አስባችኋለሁ፤ አሁን ደግሞ በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ እንድመጣ መንገድ ይከፈትልኝ ዘንድ እጸልያለሁ። እንድትጸኑ የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ አካፍላችሁ ዘንድ፣ ላያችሁ እናፍቃለሁ። ይኸውም እናንተና እኔ በእያንዳንዳችን እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው። ወንድሞች ሆይ፤ በሌሎች አሕዛብ ዘንድ እንደ ሆነልኝ፣ በእናንተም ዘንድ ፍሬ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ ዐቅጄ ሳለሁ፣ እስከ አሁን ድረስ ግን መከልከሌን እንድታውቁ እወድዳለሁ። ግሪኮች ለሆኑትና ላልሆኑት፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ ዕዳ አለብኝ፤ በሮም ለምትኖሩ፣ ለእናንተም ወንጌልን ለመስበክ የምጓጓው ለዚህ ነው። በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ ይህም በመጀመሪያ ለአይሁድ፣ ቀጥሎም ለአሕዛብ ነው። በወንጌል የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧልና፤ ጽድቁም ከእምነት ወደ እምነት የሆነ ነው፤ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው። በክፋታቸው እውነትን ዐፍነው በሚይዙ፣ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ግልጽ አድርጎታል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፣ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም። እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ፤ የዘላለም አምላክን ክብር ምዉት በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ በእንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህም እግዚአብሔር በኀጢአት በተሞላው የልባቸው ምኞት እርስ በርሳቸው የገዛ አካላቸውን እንዲያስነውሩ ቅድስና ለሌለው ሩካቤ ሥጋ አሳልፎ ሰጣቸው። የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡር አመለኩ፤ አገለገሉም፤ ፈጣሪም ለዘላለም የተመሰገነ ነው። አሜን።
ሮሜ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ሮሜ 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሮሜ 1:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች