ከዚያም ለሰባቱ መላእክት፣ “ሂዱ፤ ሰባቱን የእግዚአብሔር ቍጣ ጽዋዎች በምድር ላይ አፍስሱ” የሚል ታላቅ ድምፅ ከቤተ መቅደሱ ሰማሁ። የመጀመሪያው መልአክ ሄዶ ጽዋውን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውን ምልክት በተቀበሉትና ለምስሉም በሰገዱት ሰዎች ላይ ክፉኛ የሚያሠቃይ ቍስል ወጣባቸው። ሁለተኛው መልአክ ጽዋውን በባሕር ላይ አፈሰሰ፤ ባሕሩም እንደ ሞተ ሰው ደም ሆነ፤ በባሕሩ ውስጥ የሚኖሩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ሞቱ። ሦስተኛው መልአክ ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ላይ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። ከዚያም በውሆች ላይ ሥልጣን ያለው መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ያለህና የነበርህ ቅዱሱ ሆይ፤ እንዲህ ስለ ፈረድህ፣ አንተ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ፣ አንተም ደግሞ ደም እንዲጠጡ አደረግሃቸው፤ ይህ የሚገባቸው ነውና።” እንዲሁም ከመሠዊያው እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፤ “አዎን፤ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤ ፍርድህ እውነትና ጽድቅ ነው።” አራተኛውም መልአክ ጽዋውን በፀሓይ ላይ አፈሰሰ፤ ፀሓይም ሰዎችን በእሳት እንድታቃጥል ኀይል ተሰጣት። እነርሱም በታላቅ ሐሩር ተቃጠሉ፤ በእነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ እንጂ ንስሓ አልገቡም፤ ክብርም አልሰጡትም። ዐምስተኛውም መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም መንግሥት በጨለማ ተዋጠ፤ ሰዎችም ከሥቃያቸው የተነሣ ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር፤ ደግሞም ከሥቃያቸውና ከቍስላቸው የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ እንጂ ከሥራቸው ንስሓ አልገቡም። ስድስተኛውም መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲዘጋጅላቸው የወንዙ ውሃ ደረቀ። ከዚያም ከዘንዶው አፍ፣ ከአውሬው አፍና ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ እንቍራሪት የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ። እነርሱም ምልክቶች የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት እንዲሰበስቧቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይሄዳሉ። “እነሆ፤ እንደ ሌባ እመጣለሁ፤ ዕራቍቱን እንዳይሆን ኀፍረቱም እንዳይታይ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው ብፁዕ ነው።” እነርሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው። ሰባተኛውም መልአክ ጽዋውን በአየር ላይ አፈሰሰ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካለው ዙፋንም “ተፈጸመ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ወጣ። ከዚያም መብረቅ፣ ድምፅ፣ ነጐድጓድና ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ላይ ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ የምድር መናወጥ ታይቶ አይታወቅም፤ ነውጡም እጅግ ታላቅ ነበር። ታላቂቱ ከተማ ከሦስት ተከፈለች፤ የሕዝቦች ከተሞችም ፈራረሱ፤ እግዚአብሔርም ታላቂቱን ባቢሎን አስታወሰ፤ በብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የተሞላውን ጽዋ ሰጣት። ደሴቶች ሁሉ ሸሹ፤ ተራሮችም ሊገኙ አልቻሉም። በሚዛን ሲመዘን እያንዳንዱ አርባ ዐምስት ኪሎ ግራም የሚሆን ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ መቅሠፍቱ እጅግ አሠቃቂ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ከበረዶው መቅሠፍት የተነሣ እግዚአብሔርን ተሳደቡ።
ራእይ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ራእይ 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ራእይ 16:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች