መዝሙር 78:40-59

መዝሙር 78:40-59 NASV

በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት! በበረሓስ ምን ያህል አሳዘኑት! ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጡት። እነርሱን በዚያ ቀን ከጠላት የታደገበትን፣ ያን ኀይሉን አላስታወሱም፤ በግብጽ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት፣ በጣኔዎስም በረሓ ያሳየውን ድንቅ ሥራ አላሰቡም። ወንዞቻቸውን ወደ ደም ለወጠ፤ ከጅረቶቻቸውም መጠጣት አልቻሉም። የዝንብ ሰራዊት ሰደደባቸው፤ ነደፏቸውም፤ ጓጕንቸርም ላከባቸው፤ ሰዎችንም አጠፉ። አዝመራቸውን ለኵብኵባ፣ ሰብላቸውንም ለአንበጣ ሰጠባቸው። የወይን ተክላቸውን በበረዶ፣ የበለስ ዛፋቸውንም በውርጭ አጠፋ። ከብቶቻቸውን ለበረዶ፣ የከብት መንጋቸውን ለመብረቅ እሳት ዳረገ። ጽኑ ቍጣውን በላያቸው ሰደደ፤ መዓቱን፣ የቅናቱን ቍጣና መቅሠፍቱን ላከባቸው፤ አጥፊ የመላእክት ሰራዊትም ሰደደባቸው። ለቍጣው መንገድ አዘጋጀ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላተረፈም፤ ነገር ግን ሕይወታቸውን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጠ። የዐፍላ ጕልበታቸው መጀመሪያ የሆኑትን በካም ድንኳን፣ በኵሮቻቸውንም ሁሉ በግብጽ ምድር ፈጀ። ሕዝቡን ግን እንደ በግ አወጣቸው፤ በምድረ በዳም እንደ መንጋ መራቸው። ያለ ሥጋት መራቸው፤ እነርሱም አልፈሩም፤ ጠላቶቻቸውን ግን ባሕር ዋጣቸው። ቀኝ እጁም ወዳስገኘችው ወደዚህ ተራራ፣ ወደ ቅድስት ምድር አገባቸው። ሕዝቦችን ከፊታቸው አባረረ፤ ምድራቸውን ርስት አድርጎ በገመድ አከፋፈላቸው፤ የእስራኤልንም ነገዶች በጠላቶቻቸው ቤት አኖረ። እነርሱ ግን አምላክን ተፈታተኑት፤ በልዑልም ላይ ዐመፁ፤ ትእዛዙንም አልጠበቁም። ተመልሰው እንደ አባቶቻቸው ከዳተኛ ሆኑ፤ እንደማያስተማምን ጠማማ ቀስት ተወላገዱ። በኰረብታ ማምለኪያዎቻቸው አስቈጡት፤ ተቀርጸው በተሠሩ ጣዖቶቻቸው አስቀኑት። እግዚአብሔር ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ እስራኤልንም ፈጽሞ ተወ።