መዝሙር 37:1-40

መዝሙር 37:1-40 NASV

ዐመፀኞችን በማየት አትሸበር፤ በክፉ አድራጊዎችም አትቅና፤ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤ እንደ ለምለም ቅጠልም ይጠወልጋሉ። በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤ ጽድቅህን እንደ ብርሃን፣ ፍትሕህን እንደ ቀትር ፀሓይ ያበራዋል። በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር። ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው፤ ወደ እኵይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ። ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታሥሥ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ። ክፉዎች በጻድቃን ላይ ያሤራሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጩባቸዋል። እግዚአብሔር ግን ይሥቅባቸዋል፣ ቀናቸው እንደ ደረሰ ያውቃልና። ችግረኞችንና ድኾችን ለመጣል፣ አካሄዳቸው ቀና የሆነውንም ለመግደል፣ ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፤ ቀስታቸውንም ገተሩ። ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል፤ ቀስታቸውም ይሰበራል። የጻድቅ ጥቂት ሀብት፣ ከክፉዎች ብዙ ጥሪት ይበልጣል። የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና፣ ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ደግፎ ይይዛቸዋል። እግዚአብሔር የንጹሓንን የሕይወት ዘመን ያውቃል፤ ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል። በክፉ ጊዜ ዐንገት አይደፉም፤ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይሆናሉ፤ ይጠፋሉ፤ እንደ ጢስም ተነው ይጠፋሉ። ኀጢአተኛ ይበደራል፤ መልሶም አይከፍልም፤ ጻድቅ ግን ይቸራል። እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤ እርሱ የሚረግማቸው ግን ይጠፋሉ። የሰው አካሄድ በእግዚአብሔር ይጸናል፤ በመንገዱ ደስ ይለዋል። ቢሰናከልም አይወድቅም፣ እግዚአብሔር በእጁ ደግፎ ይይዘዋልና። ጕልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ቸር ነው፤ ያበድራልም፤ ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ። ከክፉ ራቅ፤ መልካሙንም አድርግ፣ ለዘላለምም ትኖራለህ። እግዚአብሔር ፍትሕን ይወድዳልና፣ ታማኞቹንም አይጥልም። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤ የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በርሷም ለዘላለም ይኖራሉ። የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ አንደበቱም ፍትሓዊ ነገር ያወራል። የአምላኩ ሕግ በልቡ አለ፤ አካሄዱም አይወላገድም። ክፉዎች ጻድቁን ይከታተሉታል፤ ሊገድሉትም ይሻሉ። እግዚአብሔር ግን በእጃቸው አይጥለውም፤ ፍርድ ፊት ሲቀርብም አሳልፎ አይሰጠውም። እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ። ክፉና ጨካኙን ሰው፣ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ለምልሞ አየሁት፤ ዳግመኛ በዚያ ሳልፍ፣ እነሆ፣ በቦታው አልነበረም፤ ብፈልገውም አልተገኘም። ንጹሓንን ልብ በል፤ ቅኑንም አስተውል፤ የሰላም ሰው ተስፋ አለውና። ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይጠፋሉ፤ የክፉዎችም ዘር ይወገዳል። የጻድቃን ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራ ጊዜም መጠጊያቸው እርሱ ነው። እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፤ ይታደጋቸዋልም፤ ከክፉዎች እጅ ነጥቆ ያወጣቸዋል፤ እርሱን መጠጊያ አድርገዋልና ያድናቸዋል።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}