መዝሙር 119:25-56

መዝሙር 119:25-56 NASV

ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ። ነፍሴ በሐዘን ተዝለፈለፈች፤ እንደ ቃልህ አበርታኝ። የሽንገላን መንገድ ከእኔ አርቅ፤ ሕግህን በጸጋህ ስጠኝ። የእውነትን መንገድ መርጫለሁ፤ ሕግህንም ፊት ለፊቴ አድርጌአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከምስክርነትህ ጋራ ተጣብቄአለሁ፤ አሳልፈህ ለውርደት አትስጠኝ። ልቤን አስፍተህልኛልና፣ በትእዛዞችህ መንገድ እሮጣለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ የሥርዐትህን መንገድ አስተምረኝ፤ እኔም እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ። ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ። በርሷ ደስ ይለኛልና፣ በትእዛዝህ መንገድ ምራኝ። ከራስ ጥቅም ይልቅ፣ ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል። ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ፤ በራስህ መንገድ እንደ ገና ሕያው አድርገኝ። ትፈራ ዘንድ፣ ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ፈጽም። የምፈራውን መዋረድ ከእኔ አርቅ፤ ደንብህ መልካም ነውና። እነሆ፤ ድንጋጌህን ናፈቅሁ፤ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤ ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ። በቃልህ ታምኛለሁና፣ ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ። ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እሻለሁና፣ እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ። ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም። እኔ እወድደዋለሁና፣ በትእዛዝህ ደስ ይለኛል። እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዞችህ አነሣለሁ፤ ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ። ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤ በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና። ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት። እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤ እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን አሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ። ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ ቍጣ ወረረኝ። በእንግድነቴ አገር፣ ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት። እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ ሕግህንም እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ ይህችም ተግባሬ ሆነች።