ምሳሌ 8:1-11

ምሳሌ 8:1-11 NASV

ጥበብ ጮኻ አትጣራምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አታሰማምን? በመንገድ አጠገብ ባሉ ኰረብቶች፣ መንገዶቹ በሚገናኙበትም ላይ ትቆማለች፤ ወደ ከተማዪቱ በሚያስገቡት በሮች አጠገብ፣ በመግቢያዎቹ ላይ፣ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ ስትል ትጮኻለች፤ “ሰዎች ሆይ፤ የምጠራው እኮ እናንተን ነው፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ድምፄን ከፍ አደርጋለሁ። እናንተ አላዋቂዎች፤ ጠንቃቃነትን ገንዘብ አድርጉ፤ እናንተ ሞኞች፤ ማስተዋልን አትርፉ። የምናገረው ጠቃሚ ነገር ስላለኝ አድምጡኝ፤ ቀና ነገር ለመናገር ከንፈሮቼን እከፍታለሁ። አንደበቴ እውነትን ይናገራል፤ ከንፈሮቼ ክፋትን ይጸየፋሉና። ከአንደበቴ የሚወጡት ቃሎች ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤ አንዳቸውም ጠማማና ግራ የሚያጋቡ አይደሉም። በጥልቅ ለሚያስተውሉ ሁሉም ቀና ናቸው፤ ዕውቀት ላላቸውም ስሕተት የለባቸውም። ከብር ይልቅ ምክሬን፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ ዕውቀትን ምረጡ፤ ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናትና፤ ከምትመኙት ነገር ሁሉ አንዳች የሚስተካከላት የለም።