ምሳሌ 6:23-35

ምሳሌ 6:23-35 NASV

እነዚህ ትእዛዞች መብራት ናቸውና፤ ይህችም ትምህርት ብርሃን፣ የተግሣጽ ዕርምትም የሕይወት መንገድ ናት፤ እርሷም ከምግባረ ብልሹ ሴት፣ ልዝብ አንደበት ካላት ባዕድ ሴት ትጠብቅሃለች። ውበቷን በልብህ አትመኝ፤ በዐይኗም አትጠመድ። ጋለሞታ ሴት ቍራሽ እንጀራ ታሳጣሃለችና፤ አመንዝራዪቱም በሕይወትህ በራሱ ላይ ትሸምቃለች። ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጕያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን? አንድ ሰው እግሮቹ ሳይቃጠሉ፣ በፍም ላይ መሄድ ይችላልን? ከሰው ሚስት ጋራ የሚተኛም እንደዚሁ ነው፤ የሚደርስባትም ከቅጣት አያመልጥም። ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ ሰዎች አይንቁትም። በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠይቀው ቢሆንም፣ ከተያዘ ሰባት ዕጥፍ መክፈል አለበት። የሚያመነዝር ሰው ግን ልበ ቢስ ነው፤ እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል። መደብደብና ውርደት ዕጣው ነው፤ ኀፍረቱም ከቶ አይወገድም። ቅናት የባልን ቍጣ ይቀሰቅሳልና፤ በሚበቀልበትም ጊዜ ምሕረት አያደርግም። ምንም ዐይነት ካሳ አይቀበልም፤ የቱንም ያህል ብዙ ቢሆን መማለጃን ዕሺ አይልም።