ምሳሌ 22:17-29

ምሳሌ 22:17-29 NASV

የጠቢባንን ቃል ልብ ብለህ ስማ፤ ልብህም ወደ ትምህርቴ ያዘንብል፤ በልብህ ስትጠብቃቸው፣ ሁሉም በከንፈሮችህ ላይ የተዘጋጁ ሲሆኑ ደስ ይላልና። ስለዚህ መታመኛህ በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን፣ ዛሬ አንተን ራስህን አስተምርሃለሁ። የምክርና የዕውቀት ቃል የሆኑ፣ መልካም ሠላሳ ትምህርቶችን አልጻፍሁልህምን? ለላከህ ተገቢውን መልስ ትሰጥ ዘንድ፣ እውነተኛና የታመኑ ቃሎችን እንዳስተምርህ አይደለምን? ድኾች በመሆናቸው ብቻ ድኾችን አትበዝብዛቸው፤ ችግረኛውንም በአደባባይ አታንገላታው፤ እግዚአብሔር ይፋረድላቸዋልና፤ የሚቀሟቸውንም ይቀማቸዋል። ከግልፍተኛ ጋራ ወዳጅ አትሁን፤ በቀላሉ ቱግ ከሚልም ሰው ጋራ አትወዳጅ፤ አለዚያ መንገዱን ትማራለህ፤ ራስህም ትጠመድበታለህ። በዋስትና ቃል እጅ አትምታ፤ ለብድር ተያዥ አትሁን፤ የምትከፍለው ካጣህ፣ የምትተኛበት ዐልጋ ከሥርህ ይወሰድብሃል። የቀድሞ አባቶችህ ያስቀመጡትን፣ የጥንቱን የወሰን ምልክት አታፋልስ። በሙያው ሥልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን? በነገሥታት ዘንድ ባለሟል ይሆናል፤ አልባሌ ሰዎችን አያገለግልም።