ምሳሌ 10:6-25

ምሳሌ 10:6-25 NASV

በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው፤ መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል። የጻድቃን መታሰቢያቸው በረከት ነው፤ የክፉዎች ስም ግን እንደ ጠፋ ይቀራል። በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝ ይቀበላል፤ ለፍላፊ ቂል ግን ወደ ጥፋት ያመራል። ሐቀኛ ሰው ያለ ሥጋት ይራመዳል፤ በጠማማ ጐዳና የሚሄድ ግን ይጋለጣል። በተንኰለኛ ዐይን የሚጠቅስ ሐዘን ያስከትላል፤ ለፍላፊ ቂልም ወደ ጥፋት ያመራል። የጻድቅ አንደበት የሕይወት ምንጭ ናት፤ መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል። ጥላቻ ጠብን ያነሣሣል፤ ፍቅር ግን ስሕተትን ሁሉ ይሸፍናል። ጥበብ በአስተዋይ ሰው ከንፈር ትገኛለች፤ በትር ግን ለልበ ቢስ ሰው ጀርባ ነው። ጠቢባን ዕውቀት ያከማቻሉ፤ የቂል አንደበት ግን ጥፋትን ይጋብዛል። የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ ድኽነት ግን የድኾች መጥፊያ ናት። የጻድቃን ደመወዝ ሕይወት ታስገኝላቸዋለች፤ የክፉዎች ትርፍ ግን ቅጣትን ታመጣባቸዋለች። ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ ዕርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል። ጥላቻውን የሚሸሽግ ሐሰተኛ አንደበት ያለው ነው፤ ሐሜትን የሚዘራ ሁሉ ሞኝ ነው። ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው። የጻድቅ አንደበት የነጠረ ብር ነው፤ የክፉ ሰው ልብ ግን ርባና የለውም። የጻድቃን ከንፈሮች ብዙዎችን ያንጻሉ፤ ቂሎች ግን በልበ ቢስነት ይሞታሉ። የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም። ሞኝ ሰው በክፉ ተግባር ይደሰታል፤ አስተዋይ ሰው ግን በጥበብ ደስ ይለዋል። ክፉ ሰው የፈራው ይደርስበታል፤ ጻድቅ የሚመኘው ይፈጸምለታል። ዐውሎ ነፋስ ሲነሣ ክፉዎች ተጠራርገው ይወሰዳሉ፤ ጻድቃን ግን ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።