ምሳሌ 1
1
የምሳሌዎቹ ዐላማና ጭብጥ
1የእስራኤል ንጉሥ፣ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤
2ጥበብንና ተግሣጽን ለመቀበል፤
ጥልቅ ሐሳብ የሚገልጡ ቃላትን ለማስተዋል፤
3ጽድቅን፣ ፍትሕንና ሚዛናዊ ብያኔን በማድረግ፣
የተገራ ጠቢብ ልቡናን ለማግኘት፤
4አላዋቂዎችን አስተዋይነትን፣
በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን ለመስጠት፤
5ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤
አስተዋዮችም መመሪያ ያግኙበት፤
6ይህም የጠቢባንን ምሳሌዎችና ተምሳሌቶች፣
አባባሎችና ዕንቈቅልሾች ይረዱ ዘንድ ነው።
7 እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤
ቂሎች#1፥7 በመጽሐፈ ምሳሌና በብሉይ ኪዳን ሌሎች መጻሕፍት ውስጥ ይህ ቃል በተደጋጋሚ ተጽፏል፤ የሞራል ጕድለትን ያመለክታል። ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
መግቢያ፤ ጥበብን ገንዘብ ለማድረግ የተሰጠ ምክር
ስለ ኀጢአተኞች ግብዣ ማስጠንቀቂያ
8ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ምክር አድምጥ፤
የእናትህንም ትምህርት አትተው።
9ለራስህ ሞገስን የሚያጐናጽፍ አክሊል፣
ዐንገትህን የሚያስውብ ድሪ ይሆንልሃል።
10ልጄ ሆይ፤ ኀጢአተኞች ቢያባብሉህ፣
ዕሺ አትበላቸው፤
11“ከእኛ ጋራ ናና፣ ደም ለማፍሰስ እናድባ፤
በደል በሌለበት ሰው ላይ እንሸምቅ፤
12እንደ መቃብር፣ ወደ ጕድጓድ#1፥12 በዕብራይስጡ ሲኦል ይላል። እንደሚወርዱ፣
ከነሕይወታቸው በሙሉ እንዋጣቸው፤
13ውድ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በየዐይነቱ እናገኛለን፤
ቤቶቻችንንም በዝርፊያ እንሞላለን፤
14ከእኛ ጋራ ዕጣህን ጣል፤
የጋራ ቦርሳ ይኖረናል” ቢሉህ፣
15ልጄ ሆይ፤ ዐብረሃቸው አትሂድ፤
በሚሄዱበትም መንገድ እግርህን አታንሣ፤
16እግራቸው ወደ ኀጢአት ይቸኵላል፤
ደም ለማፍሰስም ፈጣኖች ናቸው።
17ወፎች ፊት እያዩ ወጥመድ መዘርጋት፣
ምንኛ ከንቱ ነው!
18እነዚህ ሰዎች የሚያደቡት በገዛ ደማቸው ላይ ነው፤
የሚሸምቁትም በራሳቸው ላይ ብቻ ነው።
19ያላግባብ ለጥቅም የሚሯሯጡ ሁሉ መጨረሻቸው እንዲህ ነው፤
የሕይወታቸው መጥፊያም ይኸው ነው።
የጥበብ ተግሣጽ
20ጥበብ በጐዳና ላይ ጮኻ ትጣራለች፤
በየአደባባዩ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፤
21ዉካታ በበዛባቸው ጐዳናዎች ላይ#1፥21 በዕብራይስጡና በሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች በቅጥሮች ጫፍ ላይ ይላሉ። ትጮኻለች፤
በከተማዪቱም መግቢያ በር ላይ እንዲህ ትላለች፤
22“እናንተ አላዋቂዎች#1፥22 በዕብራይስጡ ብስለት የሌለው የሚለው ቃል በዚህ መጽሐፍ በአጠቃላይ መልካም ምግባር የሌለውንና ክፋትን ለማድረግ ልቡ ያዘነበለ ሰውን ያመለክታል።፤ ማስተዋል የሌለበት መንገዳችሁን እስከ መቼ ትወድዱታላችሁ?
ፌዘኞች በፌዝ ደስ የሚሰኙት፣
ሞኞችስ ዕውቀትን የሚጠሉት እስከ መቼ ነው?
23ዘለፋዬን ብትሰሙኝ ኖሮ፣
ልቤን ባፈሰስሁላችሁ፣
ሐሳቤንም ባሳወቅኋችሁ ነበር።
24ነገር ግን በተጣራሁ ጊዜ እንቢ ስላላችሁኝ፣
እጄንም ስዘረጋ ማንም ግድ ስላልነበረው፣
25ምክሬን ሁሉ ስለ ናቃችሁ፣
ዘለፋዬንም ስላልተቀበላችሁ፣
26እኔ ደግሞ በመከራችሁ እሥቅባችኋለሁ፤
መዓት በሚወርድባችሁም ጊዜ አፌዝባችኋለሁ፤
27መዓት እንደ ማዕበል ሲያናውጣችሁ፣
መከራም እንደ ዐውሎ ነፋስ ሲጠራርጋችሁ፣
ሥቃይና ችግር ሲያጥለቀልቃችሁ አፌዝባችኋለሁ።
28“በዚያ ጊዜ ይጠሩኛል፤ እኔ ግን አልመልስላቸውም፤
አጥብቀው ይፈልጉኛል፤ ነገር ግን አያገኙኝም።
29ዕውቀትን ስለ ጠሉ፣
እግዚአብሔርንም መፍራት ስላልመረጡ፣
30ምክሬን ለመቀበል ስላልፈለጉ፣
ዘለፋዬን ስለ ናቁ፣
31የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፤
የዕቅዳቸውንም ውጤት ይጠግባሉ።
32አላዋቂዎችን ስድነታቸው ይገድላቸዋል፤
ሞኞችንም መታለላቸው ያጠፋቸዋል፤
33የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤
ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል።”
Currently Selected:
ምሳሌ 1: NASV
ማድመቅ
ያጋሩ
አወዳድር
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.