እጅግ ብዙ የሆነ የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች የነበሯቸው የሮቤልና የጋድ ነገዶች የኢያዜርና የገለዓድ ምድር ለከብት ምቹ ስፍራዎች መሆናቸውን አዩ። ስለዚህ የሮቤልና የጋድ ሰዎች ወደ ሙሴ፣ ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ማኅበረ ሰቡ መሪዎች መጥተው እንዲህ አሉ፤ “አጣሮት፣ ዲቦን፣ ኢያዜር፣ ኒምራ፣ ሐሴቦን፣ ኤልያሊ፣ ሴባማ፣ ናባውና፣ ባያን፣ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ፊት እንዲሸነፍ ያደረገው ይህ ሁሉ ምድር ለከብት ምቹ ነው፤ እኛ አገልጋዮችህም ከብቶች አሉን። በፊትህ ሞገስ ያገኘን ከሆነ ይህ ምድር ለእኛ ለአገልጋዮችህ በርስትነት ይሰጠን፤ ዮርዳኖስንም እንድንሻገር አታድርገን።” ሙሴም የጋድንና የሮቤልን ነገዶች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ ወገኖቻችሁ ወደ ጦርነት ይሂዱ? እስራኤላውያን ተሻግረው እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ የምታስቈርጧቸው ለምንድን ነው? አባቶቻችሁ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። ወደ ኤሽኮል ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ካዩ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ እስራኤላውያንን ተስፋ አስቈረጧቸው። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቍጣ ነደደ፤ እንዲህም ሲል ማለ፤ ‘በፍጹም ልባቸው ስላልተከተሉኝ ከግብጽ ከወጡት፣ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች አንዳቸውም ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ ልሰጥ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም፤ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው ተከትለውታልና፣ ከቄኔዛዊው ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር አንዳቸውም አያዩዋትም።’ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ስለ ነደደ፣ በፊቱ ክፉ ነገር ያደረገው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው። “እናንተ የኀጢአተኞች ልጆች ይኸው በአባቶቻችሁ እግር ተተክታችሁ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ይበልጥ እንዲቈጣ ታደርጋላችሁ። እርሱን ከመከተል ብትመለሱ አሁንም ይህን ሁሉ ሕዝብ በምድረ በዳ ይተወዋል፤ ለሚደርስበትም ጥፋት ምክንያቱ እናንተው ትሆናላችሁ።” ከዚህ በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “እዚህ ለከብቶቻችን በረቶች፣ ለሴቶቻችንና ለልጆቻችን ከተሞች መሥራት እንወድዳለን፤ ይሁን እንጂ ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ ታጥቀንና በእስራኤላውያን ፊት ግንባር ቀደም ሆነን ለመሄድ ዝግጁ ነን፤ በዚህም ጊዜ ሴቶቻችንና ልጆቻችን በምድሪቱ ላይ ካሉት ነዋሪዎች እንዲጠበቁ በተመሸጉ ከተሞች ይኖራሉ። እኛም እያንዳንዱ እስራኤላዊ ርስቱን እስኪወርስ ድረስ ወደየቤታችን አንመለስም። ድርሻችንን ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ስላገኘን፣ ከዮርዳኖስ ማዶ ከእነርሱ ጋራ የምንካፈለው አንዳችም ርስት አይኖርም።” ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ብታደርጉ ማለትም በእግዚአብሔር ፊት ታጥቃችሁ ለጦርነት ብትዘጋጁ፣ እንዲሁም ጠላቶቹን ከፊቱ አሳድዶ እስኪያስወጣ ድረስ ሁላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ለጦርነት ዝግጁ ሆናችሁ ዮርዳኖስን ብትሻገሩ፣ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ከተገዛች በኋላ ልትመለሱ ትችላላችሁ፤ ለእግዚአብሔርና ለእስራኤል ካለባችሁም ግዴታ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህችም ምድር በእግዚአብሔር ፊት ርስታችሁ ትሆናለች። “ይህን ባታደርጉ ግን እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኀጢአታችሁ እንደሚያገኛችሁም ዕወቁ። ለሴቶቻችሁና ለልጆቻችሁ ከተሞች፣ ለበግና ለፍየል መንጎቻችሁም ጕረኖች ሥሩላቸው፤ የገባችሁበትን የተስፋ ቃል ግን ፈጽሙ።” የጋድና የሮቤል ሰዎች ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን ያዘዘንን እንፈጽማለን። ልጆቻችንና ሚስቶቻችን፣ የበግና የፍየል እንዲሁም የከብት መንጎቻችን እዚሁ በገለዓድ ከተሞች ይቀራሉ፤ ባሮችህ ግን ልክ ጌታችን እንዳለው እያንዳንዱ ሰው ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ለመዋጋት እንሻገራለን።” ከዚያም ሙሴ ለካህኑ ለአልዓዛር፣ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ነገድ ቤተ ሰብ አለቆች እነርሱን አስመልክቶ ትእዛዝ ሰጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “የጋድና የሮቤል ወንድ ሁሉ፣ እያንዳንዱ ለጦርነት በመዘጋጀት በእግዚአብሔር ፊት ከእናንተ ጋራ ዮርዳኖስን የሚሻገር ከሆነ፣ ምድሪቱም በእጃችሁ ስትገባ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ስጧቸው። ለጦርነት ተዘጋጅተው ከእናንተ ጋራ ካልተሻገሩ ግን፣ ርስታቸውን ዐብረዋችሁ በከነዓን መካፈል አለባቸው።” የጋድና የሮቤል ሰዎች እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ባሪያዎችህ እግዚአብሔር ያለውን ያደርጋሉ፤ ለጦርነት ዝግጁ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን እንሻገራለን፤ የምንወርሰው ርስት ግን ከዮርዳኖስ ወዲህ እዚሁ ይሆናል።” ከዚያም ሙሴ፣ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛትና የባሳንን ንጉሥ የዐግን ግዛት፣ ማለትም ምድሪቱንና ከነከተሞቿ በዙሪያዋ ያለውን ግዛት በሙሉ ለጋድና ለሮቤል ነገዶች እንዲሁም ለዮሴፍ ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጣቸው።
ዘኍልቍ 32 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘኍልቍ 32
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘኍልቍ 32:1-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች