ዘኍልቍ 27:12-23

ዘኍልቍ 27:12-23 NASV

ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በዓባሪም ሸንተረር ላይ ወዳለው ወደዚህ ተራራ ውጣና ለእስራኤላውያን የሰጠኋቸውን ምድር እይ። ካየኸውም በኋላ አንተም እንደ ወንድምህ እንደ አሮን ወደ ሕዝብህ ትሰበሰባለህ፤ ምክንያቱም ማኅበረ ሰቡ በጺን ምድረ በዳ ባለው ውሃ አጠገብ ባመፁ ጊዜ እኔን በሕዝቡ ፊት ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ሁለታችሁም ትእዛዜን ስላልጠበቃችሁ ነው።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኝ የመሪባ ውሃ ነው። ሙሴ እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆነ ጌታ እግዚአብሔር በዚህ ማኅበረ ሰብ ላይ ሰው ይሹም፤ እርሱም፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እንዳይሆን በፊቱ የሚወጣና የሚገባ፣ መርቶ የሚያወጣውና የሚያገባው እንዲሆን ነው።” ስለዚህም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “መንፈስ ቅዱስ ያደረበትን የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን ጫንበት። በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አድርገው፤ በፊታቸውም ሹመው፤ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ እንዲታዘዝለትም ከሥልጣንህ ከፍለህ ስጠው። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሆኖ በኡሪም በመጠየቅ ውሳኔ በሚያስገኝለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል፤ እርሱም ሆነ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ በአልዓዛር ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በርሱም ቃል ይገባሉ።” ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው የእስራኤል ማኅበር ፊት አቆመው፤ ከዚያም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘው መሠረት እጁን በራሱ ላይ ጭኖ ሾመው።