ዘኍልቍ 20:6-12

ዘኍልቍ 20:6-12 NASV

ሙሴና አሮን ከማኅበረ ሰቡ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው በግንባራቸው ተደፉ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በትሪቱን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን በአንድነት ሰብስቡ፤ እነርሱም እያዩ ዐለቱን ተናገሩት፤ ዐለቱም ውሃ ያወጣል። አንተም ለማኅበረ ሰቡ ከዐለቱ ውሃ ታወጣላቸዋለህ፤ እነርሱና ከብቶቻቸውም ይጠጣሉ።” ስለዚህም ሙሴ ልክ እንደ ታዘዘው በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ። እርሱና አሮንም ማኅበሩን በዐለቱ ፊት አንድ ላይ ሰበሰቡ፤ ሙሴም፣ “እናንተ ዐመፀኞች ስሙ፤ ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” አላቸው። ከዚያም ሙሴ እጁን ዘርግቶ በበትሩ ዐለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ውሃውም ተንዶለዶለ፤ ማኅበረ ሰቡና ከብቶቻቸውም ጠጡ። ነገር ግን እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን፣ “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ስላልታመናችሁብኝ ይህን ማኅበረ ሰብ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም” አላቸው።