ዘኍልቍ 17:1-11

ዘኍልቍ 17:1-11 NASV

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን ንገራቸውና ከየነገዱ አለቆች አንዳንድ፣ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት በትር ተቀበል፤ የያንዳንዱንም ሰው ስም በየበትሩ ላይ ጻፈው። ለያንዳንዱ የነገድ አለቃ አንዳንድ በትር መኖር ስላለበት በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ። በትሮቹንም እኔ ከአንተ ጋራ በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ ፊት ለፊት አስቀምጣቸው። እኔ የምመርጠው ሰው በትርም ታቈጠቍጣለች፤ እስራኤላውያን በእናንተ ላይ ነጋ ጠባ የሚያደርጉትንም ማጕረምረም በዚህ እገታለሁ።” ሙሴም ለእስራኤላውያን ተናገራቸው፤ አለቆቻቸውም በቀደሙት በእያንዳንዱ አባቶች ስም ዐሥራ ሁለት በትር ሰጡት፤ የአሮን በትርም በበትሮቹ መካከል ነበረች። ሙሴም በትሮቹን ወስዶ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት አኖራቸው። በማግስቱም ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ሲገባ በሌዊ ቤት ስም የቀረበችው የአሮን በትር ማቈጥቈጥ ብቻ ሳይሆን እንቡጥ አውጥታ፣ አብባና አልሙን አፍርታ አገኛት። ከዚያም ሙሴ በትሮቹን ከእግዚአብሔር ፊት አውጥቶ ወደ እስራኤላውያን ሁሉ አመጣቸው፤ እነርሱም አዩ፤ እያንዳንዱም ሰው የየራሱን በትር ወሰደ። እግዚአብሔር ሙሴን፣ “የአሮን በትር ለዐመፀኞቹ ምልክት እንድትሆን መልሰህ በምስክሩ ፊት ለፊት አኑራት፤ እነርሱ እንዳይሞቱም በእኔ ላይ የሚያደርጉትን ማጕረምረም ይህ ይገታዋል” አለው። ሙሴም ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።