ዘኍልቍ 14:1-39

ዘኍልቍ 14:1-39 NASV

በዚያች ሌሊት ማኅበረ ሰቡ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸና አለቀሰ። እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሏቸው፤ “ምነው በግብጽ ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እግዚአብሔር ወደዚህች ምድር የሚያመጣን ለምንድን ነው? በሰይፍ እንድንወድቅ ነውን? ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ታዲያ ወደ ግብጽ መመለሱ አይሻለንም?” እርስ በርሳቸውም፣ “አለቃ መርጠን ወደ ግብጽ እንመለስ” ተባባሉ። ከዚያም ሙሴና አሮን እዚያ በተሰበሰቡት በመላው እስራኤላውያን ማኅበር ፊት በግንባራቸው ተደፉ። ምድሪቱን ከሰለሏት መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ለመላው የእስራኤል ማኅበርም እንዲህ አሉ፤ “ዞረን ያየናትና የሰለልናት ምድር እጅግ ሲበዛ መልካም ናት። እግዚአብሔር በእኛ ደስ ከተሠኘብን ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደዚያች ምድር መርቶ ያገባናል፤ ለእኛም ይሰጠናል። ብቻ በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሯቸው። ጥላቸው ተገፍፏል፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋራ ነውና አትፍሯቸው።” መላው ማኅበር ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተነጋገሩ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ክብር በመገናኛው ድንኳን ለእስራኤላውያን ሁሉ ተገለጠ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው? በቸነፈር እመታዋለሁ፤ እደመስሰዋለሁም፤ አንተን ግን ብርቱና ታላቅ ለሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” ሙሴ እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ነገሩን ግብጻውያን ቢሰሙትስ! ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከመካከላቸው አውጥተኸዋልና፤ የተደረገውንም በዚች ምድር ለሚኖሩት ሰዎች ይነግሯቸዋል። እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋራ መሆንህን፣ ደግሞም አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊት ለፊት እንደ ታየህና ደመናህ በላያቸው እንደ ሆነ፣ አንተም ቀን በደመና ዐምድ ሌሊትም በእሳት ዐምድ እፊት እፊታቸው እየሄድህ እንደ መራሃቸው ቀድሞውኑ ሰምተዋል። ታዲያ ይህን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ብትፈጀው ዝናህን የሰሙ ሕዝቦች፣ ‘እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ ይሰጠው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባለት ምድር ሊያስገባው ባለመቻሉ በምድረ በዳ ፈጀው’ ይሉሃል። “አሁንም እንዲህ ስትል በተናገርኸው መሠረት የጌታ ኀይል ይገለጥ፤ ‘እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’ ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው ሁሉ እንደ ፍቅርህ ታላቅነት መጠን እባክህ አሁንም የዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።” እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር ብያቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ ሕያው እንደ መሆኔና የእግዚአብሔርም ክብር ምድርን ሁሉ የሞላ እንደ መሆኑ መጠን፣ ክብሬን ደግሞም በግብጽና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ታምራት አይተው ካልታዘዙኝና ዐሥር ጊዜ ከተፈታተኑኝ ሰዎች አንዳቸውም፣ ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም። የናቀኝ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ አያያትም፤ አገልጋዬ ካሌብ ግን የተለየ መንፈስ ስላለውና በፍጹም ልቡ የተከተለኝ በመሆኑ ሄዶባት ወደ ነበረችው ምድር አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ይወርሷታል። አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው የሚኖሩ ስለ ሆነ በነገው ዕለት ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።” እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ክፉ ማኅበረ ሰብ በእኔ ላይ የሚያጕረመርመው እስከ መቼ ነው? የእነዚህን ነጭናጮች እስራኤላውያን ማጕረምረም ሰምቻለሁ። ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ስትናገሩ የሰማኋችሁን እነዚያን ነገሮች አደርግባችኋለሁ፤ በተደረገው ቈጠራ መሠረት፣ ሃያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናችሁና በእኔም ላይ ያጕረመረማችሁ ሁሉ በድናችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል። መኖሪያችሁ እንድትሆን በጽኑ ወደማልሁላችሁ ምድር ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእናንተ አንዳችሁም አትገቡባትም። ይማረካሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን ግን አገባቸዋለሁ፤ እናንተ የናቃችኋትን ምድር እነርሱ ይደሰቱባታል። እናንተ ግን፣ በድናችሁ በዚሁ ምድረ በዳ ወድቆ ይቀራል። ካለማመናችሁ የተነሣ ከእናንተ የመጨረሻው በድን እዚሁ ምድረ በዳ እስኪወድቅ ድረስ፣ ልጆቻችሁ መከራ እየበሉ አርባ ዓመት እረኞች ይሆናሉ። ምድሪቱን ለመሰለል በቈያችሁበት አርባ ቀን ልክ እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዕለት ተቈጥሮ ስለ ኀጢአታችሁ አርባ ዓመት መከራ ትቀበላላችሁ፤ ምን ያህል በእናንተ ላይ እንደ ተነሣሁም ታውቃላችሁ።’ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም አንድ ሆኖ በተነሣብኝ በዚህ ክፉ ማኅበረ ሰብ ሁሉ ላይ እነዚህን ነገሮች አደርጋለሁ፤ መጨረሻቸው በዚሁ ምድረ በዳ ይሆናል፤ እዚሁም ይሞታሉ።” ከዚህ በኋላ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ ልኳቸው የነበሩትና ከዚያ ተመልሰው ስለ ምድሪቱ ክፉ ወሬ በማሠራጨት ማኅበረ ሰቡ በሙሉ እንዲያጕረመርሙበት ያደረጉ፣ ስለ ምድሪቱም ክፉ ወሬ በማሠራጨት ተጠያቂ የሆኑት እነዚሁ ሰዎች ተቀሥፈው በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ። ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከተላኩት ሰዎች በሕይወት የተረፉት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ብቻ ነበሩ። ሙሴም ይህን ለእስራኤላውያን ሁሉ በነገራቸው ጊዜ ክፉኛ ዐዘኑ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}