ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ። “ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል። አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ። ሰማያትን፣ ከሰማያት በላይ ያሉትን ሰማያትና የከዋክብታቸውን ሰራዊት ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያለውን ሁሉ፣ ባሕሮችንና በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ፤ የሰማይ ሰራዊትም ይሰግዱልሃል። “አብራምን የመረጥኸውና ከከለዳውያን ዑር አውጥተህ አብርሃም የሚል ስም የሰጠኸው አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ። ልቡ ለአንተ የታመነ ሆኖ ስላገኘኸውም፣ የከነዓናውያንን የኬጢያውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የጌርጌሳውያንን ምድር ለዘሮቹ ለመስጠት ከርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገባህ፤ ጻድቅ ስለ ሆንህም የሰጠኸውን ተስፋ ጠበቅህ። “አንተ በግብጽ የአባቶቻችንን ሥቃይ አየህ፤ በቀይ ባሕርም ጩኸታቸውን ሰማህ። ታምራታዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በፈርዖንና፣ በሹማምቱ ሁሉ፣ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ላክህ፤ ይህንም ያደረግኸው ግብጻውያን እንዴት በእብሪት እንዳስጨነቋቸው ስላወቅህ ነው። እስከ ዛሬም የሚጠራ ስም ለራስህ እንዲኖርህ አደረግህ። በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ ባሕሩን በፊታቸው ከፈልህ፤ ያሳደዷቸውን ግን በኀይለኛ ውሃ ውስጥ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ውስጥ ወረወርሃቸው። ቀን በደመና ዐምድ፣ በሚሄዱበት መንገድ ታበራላቸውም ዘንድ ሌሊት በእሳት ዐምድ መራሃቸው። “በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው። ትክክለኛ ደንቦችንና እውነተኛ ሕጎችን፣ መልካም ሥርዐቶችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው። የተቀደሰች ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፤ ትእዛዞችን፣ ሥርዐቶችንና ሕጎችን በባሪያህ በሙሴ አማካይነት ሰጠሃቸው። በተራቡ ጊዜ ከሰማይ መና ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ከዐለት ውሃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው በተዘረጋች እጅ ወደማልህላቸውም ምድር ገብተው እንዲወርሱ አዘዝሃቸው። “እነርሱና አባቶቻችን ግን ትምክሕተኞችና ዐንገተ ደንዳኖች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም። ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አቅልጠው፣ ‘ከግብጽ ያወጣህ አምላክ ይህ ነው’ ባሉና አስጸያፊ የስድብ ቃል በተናገሩ ጊዜ እንኳ አልተለየሃቸውም።
ነህምያ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ነህምያ 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ነህምያ 9:5-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች