ከዚያም አገረ ገዥው ነህምያ፣ ካህኑና ጸሓፊው ዕዝራ፣ ሕዝቡንም የሚያስተምሩት ሌዋውያን፣ “ይህች ቀን ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተቀደሰች ናት፤ አትዘኑ፤ አታልቅሱም” አሏቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሚሰሙበት ጊዜ ያለቅሱ ነበር። ነህምያም፣ “ሂዱ፤ ጥሩ ምግብ በመብላት፣ ጣፋጩን በመጠጣት ደስ ይበላችሁ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ካላችሁ ላይ ከፍላችሁ ላኩላቸው። ይህች ቀን ለጌታችን የተቀደሰች ናት፤ የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው። ሌዋውያኑም፣ “ይህች ቀን የተቀደሰች ስለ ሆነች ዝም በሉ፤ አትዘኑም” በማለት ሕዝቡን ሁሉ አረጋጉ። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ የተነገራቸውን ቃል ተረድተው ስለ ነበረ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ከምግባቸው ከፍለው ለመላክና ሐሤትም ለማድረግ ሄዱ። ከወሩም በሁለተኛው ቀን የየቤተ ሰቡ ሁሉ ኀላፊዎች፣ የሕጉን ቃል ለመማር ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋራ በጸሓፊው በዕዝራ ዙሪያ ተሰበሰቡ። እስራኤላውያን በሰባተኛው ወር በሚውለው በዓል በዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን ትእዛዝ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤ ስለዚህ በየከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌም ይህን ቃል እንዲያውጁና እንዲያሠራጩ እንዲህ በማለት አዘዟቸው፤ “ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ ከዘይትና ከበረሓ ወይራ፣ ከባርሰነት፣ ከዘንባባና ከለምለም ዛፎች ቅርንጫፎችን አምጡ፤ በተጻፈው መሠረት ዳሶችን ሥሩ።” ስለዚህ ሕዝቡ ወጥተው ቅርንጫፎች አመጡ፤ እያንዳንዳቸውም በየቤታቸው ጣራ ሰገነት፣ በየግቢያቸው፣ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፣ “በውሃ በር” አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠሩ። ከምርኮ የተመለሰውም ማኅበር ሁሉ ዳሱን ሠርቶ ተቀመጠ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን እንደዚያ አድርገው በዓሉን አክብረው አያውቁም፤ ደስታቸውም ታላቅ ነበር። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ፣ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። እነርሱም በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ተደረገ።
ነህምያ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ ነህምያ 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ነህምያ 8:9-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች