ነህምያ 6:5-9

ነህምያ 6:5-9 NASV

ከዚያም ሰንባላጥ ለዐምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት በረዳቱ ላከብኝ፤ በእጁም ማኅተም የሌለው ያልታሸገ ደብዳቤ ይዞ ነበር፤ የተጻፈበትም እንዲህ የሚል ነበር፤ “አንተና አይሁዳውያን ለማመፅ እንደምትዶልቱና ቅጥሩንም እንደምትሠሩ በሕዝቦች መካከል ተወርቷል፤ ጌሳምም እውነት መሆኑን አረጋግጧል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተወራው መሠረት አንተ ንጉሣቸው እንደምትሆን፣ ስለ አንተም ‘በአይሁድ ንጉሥ አለ’ ብለው በኢየሩሳሌም የሚያውጁ ነቢያትን እንኳ ሳይቀር እንደ ሾምህ ተወርቷል፤ ይህም ነገር ለንጉሡ መድረሱ አይቀርም፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።” እኔም “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” ብዬ መልስ ላክሁበት። ሁሉም፣ “እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል” ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ። እኔ ግን፣ “አሁንም እጄን አበርታ” ስል ጸለይሁ።