ነህምያ 6:1-14

ነህምያ 6:1-14 NASV

እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለበሮቹ መዝጊያ ባልገጥምላቸውም እንኳ፣ ቅጥሩን መሥራቴንና የቀረ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረባዊው ጌሳምና የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ ሰንባላጥና ጌሳም፣ “ናና በኦኖ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንገናኝ” ሲሉ ይህችን መልእክት ላኩብኝ። እነርሱ ግን እኔን ለመጕዳት ዐቅደው ነበር። እኔም፣ “ታላቅ ሥራ እየሠራሁ ስለ ሆነ፣ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ትቼው ወደ እናንተ ወርጄ ሥራው ለምን ይቆማል?” በማለት ይህን መልስ የሚያደርሱ መልእክተኞችን ወደ እነርሱ ላክሁ። አራት ጊዜም ይህንኑ ዐይነት መልእክት ላኩብኝ፤ እኔም በእያንዳንዱ ጊዜ ያንኑ መልስ ሰጠሁ። ከዚያም ሰንባላጥ ለዐምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት በረዳቱ ላከብኝ፤ በእጁም ማኅተም የሌለው ያልታሸገ ደብዳቤ ይዞ ነበር፤ የተጻፈበትም እንዲህ የሚል ነበር፤ “አንተና አይሁዳውያን ለማመፅ እንደምትዶልቱና ቅጥሩንም እንደምትሠሩ በሕዝቦች መካከል ተወርቷል፤ ጌሳምም እውነት መሆኑን አረጋግጧል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተወራው መሠረት አንተ ንጉሣቸው እንደምትሆን፣ ስለ አንተም ‘በአይሁድ ንጉሥ አለ’ ብለው በኢየሩሳሌም የሚያውጁ ነቢያትን እንኳ ሳይቀር እንደ ሾምህ ተወርቷል፤ ይህም ነገር ለንጉሡ መድረሱ አይቀርም፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።” እኔም “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” ብዬ መልስ ላክሁበት። ሁሉም፣ “እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል” ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ። እኔ ግን፣ “አሁንም እጄን አበርታ” ስል ጸለይሁ። አንድ ቀን ቤቱ በላዩ ላይ ተዘግቶበት ወደ ነበረው ወደ መሄጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ሄድሁ፤ እርሱም፣ “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በርግጥም በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው” አለኝ። እኔ ግን፣ “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ ይደበቃል? ወይም ደግሞ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” አልሁ። በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦቢያና ሰንባላጥ በገንዘብ ስለ ደለሉት እንጂ እግዚአብሔር ወደ እኔ እንዳልላከው ተረዳሁ። በገንዘብ የተገዛው እኔን ለማስፈራራት ነው፤ ይኸውም ይህን በመፈጸም ኀጢአት እንድሠራና በዚህም መጥፎ ስም ሰጥተው ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ለማድረግ ነው። አምላኬ ሆይ፤ ስለ ፈጸሙት ድርጊት ጦቢያንና ሰንባላጥን ዐስብ፤ ሊያስፈራሩኝ የሞከሩትን ነቢያቱን ኖዓድያንና ሌሎቹን ነቢያትም ዐስብ።