የዓሣ በሩን የሃስናአ ልጆች ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ። የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ያለውን የሜሴዜቤል ልጅ የቤራክያ ልጅ ሜሱላም መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ያለውን የበዓና ልጅ ሳዶቅ መልሶ ሠራ፤ የሚቀጥለውን ክፍል የቴቁሔ ሰዎች መልሰው ሠሩ፤ መኳንንታቸው ግን በተቈጣጣሪ አሠሪዎቻቸው ሥር ሆነው በሥራው መጠመድ አልፈለጉም። አሮጌውን በር የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም መልሰው ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ ማያያዣዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የዕድሳቱ ሥራ የተከናወነው በኤፍራጥስ ማዶ በሚገኘው አገረ ገዥ ሥልጣን ሥር ባሉት በገባዖንና በምጽጳ ሰዎች በገባዖናዊው በመልጥያና በሜሮኖታዊው በያዶን ነበር። ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ የሆነው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል የሚቀጥለውን ክፍል ሠራ፤ ከሽቱ ቀማሚዎች አንዱ የሆነው ሐናንያ ደግሞ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። እነርሱም ሰፊው ቅጥር ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ኢየሩሳሌምን መልሰው ሠሩ። ከዚያ የሚቀጥለውን ክፍል የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሑር ልጅ ረፋያ መልሶ ሠራ። የኤርማፍ ልጅ ይዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ፤ የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ ደግሞ ከርሱ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። የካሪም ልጅ መልክያና የፈሐት ሞዓብ ልጅ አሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶን ግንብ ተብሎ የሚጠራውን መልሰው ሠሩ። የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የአሎኤስ ልጅ ሰሎም ከሴት ልጆቹ ጋራ በመሆን ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። “የሸለቆ በር” ተብሎ የሚጠራውን የሐኖንና የዛኖ ነዋሪዎች ዐደሱት፤ መልሰው ሠሩት፤ ከሠሩትም በኋላ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጁ። እንዲሁም የቈሻሻ መጣያ በር ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን አንድ ሺሕ ክንድ ቅጥር መልሰው ሠሩ። የቈሻሻ መጣያ በር ተብሎ የሚጠራው የቤትሐካሪም አውራጃ ገዥ የሆነው የሬካብ ልጅ መልክያ መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራ በኋላም መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖረ። የምጽጳ አውራጃ አለቃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም “የምንጭ በር” ተብሎ የሚጠራውን መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራም በኋላ ከድኖ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖረ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጀ። የንጉሥ አትክልት ቦታ ተብሎ በሚጠራው አጠገብ የሚገኘውን የሼላን መዋኛ ግንብም፣ ከዳዊት ከተማ ጀምሮ ቍልቍል እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ መልሶ ሠራ።
ነህምያ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ነህምያ 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ነህምያ 3:3-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች