እኔም ወደ ኢየሩሳሌም ሄድሁ፤ በዚያም ሦስት ቀን ከቈየሁ በኋላ፣ ከጥቂት ሰዎች ጋራ በሌሊት ወጣሁ። ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ አምላኬ በልቤ ያኖረውን ነገር ለማንም አልነገርሁም፤ ከተቀመጥሁበት እንስሳ በቀር ከእኔ ጋራ ሌሎች እንስሳት አልነበሩም። በሌሊትም ወጥቼ በሸለቆው በር በኩል አድርጌ ወደ ዘንዶው የውሃ ጕድጓድና ወደ ቈሻሻ መድፊያው በር ሄድሁ፤ የፈረሱትንም የኢየሩሳሌምን ቅጥሮችና በእሳት የወደሙትን በሮች ተመለከትሁ። ከዚያም ወደ ውሃ ምንጭ በርና ወደ ንጉሡ ኵሬ ሄድሁ፤ ይሁን እንጂ የተቀመጥሁበትን እንስሳ ማሳለፍ የሚያስችል በቂ ቦታ አልነበረም። ስለዚህ ቅጥሩን እየተመለከትሁ ሌሊቱን ሸለቆውን ዐልፌ ወደ ላይ ወጣሁ፤ በመጨረሻም ተመልሼ በሸለቆው በር በኩል ገባሁ። ለአይሁድ ወይም ለካህናቱ ወይም ለመኳንንቱ ወይም ለሹማምቱ ወይም ሥራውን ለሚሠሩት ሰዎች ገና ምንም የተናገርሁት ነገር ስላልነበረ፣ ወዴት እንደ ሄድሁ ወይም ምን እንዳደረግሁ ሹማምቱ አላወቁም። ከዚያም፣ “ያለንበትን ችግር ይኸው ታያላችሁ፤ ኢየሩሳሌም ፈርሳለች፤ በሮቿም በእሳት ጋይተዋል፤ አሁንም ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደ ገና እንሥራ፤ ከእንግዲህስ መሣለቂያ አንሆንም” አልኋቸው። እንዲሁም መልካሚቱ የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ እንደ ነበረችና ንጉሡም ምን እንዳለኝ ነገርኋቸው። እነርሱም፣ “እንደ ገና መሥራቱን እንጀምር!” ካሉ በኋላ ይህን መልካም ሥራ ጀመሩ። ነገር ግን ሖሮናዊው ሰንባላጥ፣ አሞናዊው ሹም ጦቢያና ዐረባዊው ጌሳም ይህን ሲሰሙ አፌዙብን፤ አንቋሸሹንም፤ እንዲሁም፣ “የምታደርጉት ይህ ምንድን ነው? በንጉሡ ላይ ልታምፁ ትፈልጋላችሁን?” አሉ። እኔም፣ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛ ባሪያዎቹ እንደ ገና ሥራውን እንጀምራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ድርሻ ወይም ይገባናል የምትሉት ወይም የታሪክ መታሰቢያ የላችሁም” ስል መለስሁላቸው።
ነህምያ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ነህምያ 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ነህምያ 2:11-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች