ማርቆስ 9:30-37

ማርቆስ 9:30-37 NASV

ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል ዐለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ለደቀ መዛሙርቱ፣ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር። እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ቤት ከገባ በኋላም፣ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ። ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው። አንድ ሕፃን አምጥቶም በመካከላቸው አቆመ፤ ዐቅፎትም፣ “ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ማንም ቢኖር የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች