ማርቆስ 9:14-24

ማርቆስ 9:14-24 NASV

ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከብበዋቸው፣ የኦሪት ሕግ መምህራን ከእነርሱ ጋራ ሲከራከሩ አዩ። ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ። እርሱም፣ “ከእነርሱ ጋራ የምትከራከሩት ስለ ምን ጕዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ ዐድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ ዐረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፣ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት።” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፣ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፣ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ጮኸ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች