ማርቆስ 7:14-23

ማርቆስ 7:14-23 NASV

ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤ ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤ [ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።”] ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እርሱም፣ “እናንተም አይገባችሁምን? ከውጭ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤ ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ይገባል፤ ከዚያም ከሰውነቱ ይወጣልና።” ኢየሱስ ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጠ። ቀጥሎም፣ እንዲህ አለ፤ “ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፤ ከውስጥ፣ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፣ ምንዝር፣ ስርቆት፤ ሰው መግደል፣ ዝሙት፣ መስገብገብ፣ ክፋት፣ ማታለል፣ መዳራት፣ ምቀኛነት፣ ስም ማጥፋት፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው። እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከውስጥ ይወጣሉ፤ ሰውንም ያረክሱታል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች