ማርቆስ 4:26-34

ማርቆስ 4:26-34 NASV

ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ ምድርም ራሷ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ ዐጨዳ ይጀምራል።” ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋራ እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትልልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።” ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው። ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች