ኢየሱስም ዳግም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጣ፤ ሕዝቡም በብዛት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም አስተማራቸው። በዚያም ሲያልፍ የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መሰብሰቢያው ስፍራ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው። በሌዊም ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች ተከትለውት ስለ ነበር፣ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ዐብረው ይመገቡ ነበር። የፈሪሳውያን ጸሐፍት ከኀጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋራ ሲበላ ባዩት ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋራ ለምን ይበላል?” ሲሉ ጠየቋቸው። ኢየሱስም የሚናገሩትን ሰምቶ፣ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም፤ እኔ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁም” አላቸው። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር፤ አንዳንድ ሰዎችም መጥተው ኢየሱስን፣ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ሲጾሙ፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋራ እያለ ዕድምተኞቹ ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋራ እያለ ሊጾሙ አይችሉም፤ ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያም ጊዜ ይጾማሉ። “በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ቍራጭ ጨርቅ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፣ አዲሱ ጨርቅ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሰፋል። እንዲሁም አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ የሚያስቀምጥ የለም፤ ይህ ከተደረገማ የወይን ጠጁ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም አቍማዳውም ይበላሻሉ። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ መቀመጥ ያለበት በአዲስ አቍማዳ ነው።” በሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ሲያልፍ፣ ዐብረውት በመጓዝ ላይ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። ፈሪሳውያንም፣ “እነሆ፤ በሰንበት ቀን ለምን ያልተፈቀደውን ነገር ያደርጋሉ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊት በተራበና የምግብ ፍላጎት በጸናበት ጊዜ ዐብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋራ ያደረገውን አላነበባችሁምን? በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፣ ካህናት ብቻ እንዲበሉት የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ለርሱም ሆነ ዐብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ፣ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም፤ ስለዚህ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው።”
ማርቆስ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 2:13-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች