ሰንበት ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው የኢየሱስን ሥጋ ለመቀባት ሽቱ ገዙ። በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጧት በማለዳ፣ ገና ፀሓይ እንደ ወጣች፣ ወደ መቃብሩ በመሄድ ላይ ሳሉ፣ “ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ላይ ማን ያንከባልልልናል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ቀና ብለው ሲመለከቱ፣ በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከደጃፉ ላይ ተንከባልሎ አዩ። ወደ መቃብሩ እንደ ገቡም፣ ነጭ ልብስ የለበሰ ጕልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጉታላችሁ፤ እርሱ ግን ተነሥቷል! እዚህ የለም፤ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውላችሁ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፣ ‘ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደ ነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ሴቶቹም እየተንቀጠቀጡና እየተደነቁ ከመቃብሩ ሸሽተው ወጡ፤ ፈርተው ስለ ነበር ለማንም አንዳች አልተናገሩም። [በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ማለዳ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለማርያም መግደላዊት በመጀመሪያ ታየ። እርሷም ሄዳ፣ ከርሱ ጋራ የነበሩት እያዘኑ ሲያለቅሱ አግኝታ ነገረቻቸው፤ እነርሱ ግን እርሱ ሕያው መሆኑንና ለርሷም መታየቱን ሲሰሙ አላመኗትም። ከዚህ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ ወደ ገጠር ሲሄዱ በሌላ መልክ ታያቸው። እነርሱም ተመልሰው ይህንኑ ለቀሩት ነገሯቸው፤ ይሁን እንጂ እነርሱንም አላመኗቸውም። ከዚያም ዐሥራ አንዱ በማእድ ላይ ሳሉ ተገለጠላቸው፤ ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች የነገሯቸውን ስላላመኗቸው፣ አለማመናቸውንና የልባቸውን ድንዳኔ ነቀፈ። እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ።” ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው፣ በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋራ ይሠራ ነበር፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።]
ማርቆስ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 16:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች