ማርቆስ 15:33-47

ማርቆስ 15:33-47 NASV

ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ። ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ ከዚያም፣ “ተዉት፤ እስኪ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አለ። በዚህ ጊዜ ሴቶች ከሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፣ እንዲሁም ሰሎሜ ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች በገሊላ ሲከተሉትና ሲያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ደግሞም ዐብረውት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ። ጊዜው እየመሸ መጥቶ የሰንበት ዋዜማ ይኸውም የመዘጋጀት ቀን ሆነ፤ የተከበረ የሸንጎ አባልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲህ በቶሎ መሞቱን ሲሰማ ተደነቀ፤ የመቶ አለቃውንም ወደ ራሱ ጠርቶ ከሞተ ምን ያህል ጊዜ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ መሞቱንም ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላ ሥጋውን ለዮሴፍ ሰጠው። ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ ሥጋውንም አውርዶ በበፍታው ከከፈነው በኋላ፣ ከዐለት በተወቀረ መቃብር አኖረው፤ የመቃብሩንም ደጃፍ በድንጋይ ገጠመው። ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያም የት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች