ወዲያውም በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፣ ከጸሐፍትና ከመላው የሸንጎ አባላት ጋራ ከተማከሩ በኋላ፣ ኢየሱስን አስረው ወሰዱት፤ ለጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም፣ “አንተው አልኸው፣” በማለት መለሰለት። የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት። ጲላጦስም፣ “ለምን መልስ አትሰጥም? እነሆ፤ በብዙ ነገር ከስሰውሃል” ሲል እንደ ገና ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰም፤ ጲላጦስ ተገረመ። በበዓል ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን እስረኛ የመልቀቅ ልማድ ነበር። በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋራ የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ሕዝቡም መጥተው እንደተለመደው እንዲያደርግላቸው ለመኑት። ጲላጦስም፣ “የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው፤ ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ። ጲላጦስም እንደ ገና፣ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም እንደ ገና፣ “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ” አላቸው። እነርሱ ግን፣ “ስቀለው!” እያሉ የባሰ ጮኹ። ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሠኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮቹ ፕራይቶሪዮን ወደ ተባለ ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ። ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ ደፉበት። ከዚያም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ እጅ ነሡት፤ ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም ኢየሱስን፣ ትርጕሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደ ተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። ከከርቤ ጋራ የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ። ሲሰቅሉትም ጊዜው ከጧቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሑፍም፣ የአይሁድ ንጉሥ የሚል ነበር። ከርሱም ጋራ ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ። [መጽሐፍ፣ “ከዐመፀኞች ጋራ ተቈጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ።] በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አዪ፤ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ፤ እስኪ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!” እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ፣ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስኪ ከመስቀል ይውረድ።” ከርሱ ጋራ የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ። ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ ከዚያም፣ “ተዉት፤ እስኪ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አለ። በዚህ ጊዜ ሴቶች ከሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፣ እንዲሁም ሰሎሜ ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች በገሊላ ሲከተሉትና ሲያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ደግሞም ዐብረውት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ። ጊዜው እየመሸ መጥቶ የሰንበት ዋዜማ ይኸውም የመዘጋጀት ቀን ሆነ፤ የተከበረ የሸንጎ አባልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲህ በቶሎ መሞቱን ሲሰማ ተደነቀ፤ የመቶ አለቃውንም ወደ ራሱ ጠርቶ ከሞተ ምን ያህል ጊዜ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ መሞቱንም ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላ ሥጋውን ለዮሴፍ ሰጠው። ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ ሥጋውንም አውርዶ በበፍታው ከከፈነው በኋላ፣ ከዐለት በተወቀረ መቃብር አኖረው፤ የመቃብሩንም ደጃፍ በድንጋይ ገጠመው። ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያም የት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።
ማርቆስ 15 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 15
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 15:1-47
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች