ማርቆስ 14:17-26

ማርቆስ 14:17-26 NASV

በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ፣ ዐብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም ዐዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፣ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፣ ከእኔ ጋራ እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “ዕንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ከወይን ፍሬ አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።