ከዚያም እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው ወይን ተከለ፤ ዙሪያውን ዐጠረ፤ ለመጭመቂያው ጕድጓድ ቈፈረ፤ የመጠበቂያም ማማ ሠራለት፤ ለገበሬዎችም አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። በመከር ጊዜም ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት ባሪያውን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። እነርሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት። እንደ ገናም ሌላ ባሪያ ላከ። እነርሱም ራሱን ፈንክተውና አዋርደው መለሱት። አሁንም እንደ ገና ሌላ ላከ፤ ይህኛውንም ገደሉት፤ ከሌሎች ከብዙዎቹ መካከል አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹንም ገደሉ። “አሁንም የሚላክ ሌላ ነበረው፤ እርሱም የሚወድደው ልጁ ነበረ፤ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ከሁሉ በኋላ ላከው። “ገበሬዎቹ ግን እርስ በርሳቸው፣ ‘ይህማ ዋናው ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው፤ ርስቱ የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ፤ ከዚያም ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ስፍራም አውጥተው ጣሉት። “እንግዲህ የወይኑ አትክልት ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣል፤ ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። እንዲህ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን? “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ፤ ጌታ ይህን አድርጓል፣ ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’” ምሳሌውን የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ስላወቁ፣ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ትተዉት ሄዱ። ከዚያም በነገር እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛ ሰው መሆንህን፣ ለማንም ሳታደላ ሁሉንም እኩል እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም? እኛስ እንክፈል ወይስ አንክፈል?” ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ፣ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስኪ አንድ ዲናር አምጡልኝና ልየው” አላቸው። እነርሱም አመጡለት፣ “ይህ የማን መልክ ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት። ኢየሱስም፣ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በርሱ እጅግ ተደነቁ። ከዚህ በኋላ ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ የአንድ ሰው ወንድም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ የሟችን ሚስት አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው አግብቷት ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሁለተኛውም ሴትዮዋን አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች። እንግዲህ፣ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሣኤ ለማንኛቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ የምትስቱ አይደለምን? ሙታን በሚነሡበት ጊዜ እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም። ስለ ሙታን መነሣት ግን፣ በሙሴ መጽሐፍ ይኸውም ስለ ቍጥቋጦው በተነገረው ክፍል፣ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ያለውን አላነበባችሁምን? እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ እጅግ ተሳስታችኋል!”
ማርቆስ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 12:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች