ማቴዎስ 9:20-38

ማቴዎስ 9:20-38 NASV

ከዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት ከበስተኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች። እርሷም በልቧ፣ “የልብሱን ጫፍ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” ብላ ነበር። ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ “አይዞሽ፣ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ተፈወሰች። ኢየሱስ ወደ ሹሙ ቤት እንደ ደረሰ እንቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፣ “ዞር በሉ፤ ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው፤ እነርሱ ግን ሣቁበት። ሕዝቡም ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዘ፤ ብላቴናዪቱም ተነሥታ ቆመች። ወሬውም በአካባቢው ሁሉ ተሠራጨ። ኢየሱስም ከዚያ እንደ ሄደ ሁለት ዐይነ ስውሮች፣ “የዳዊት ልጅ፤ ማረን!” በማለት እየጮኹ ተከተሉት። ዐይነ ስውሮቹም ኢየሱስ ወደ ገባበት ቤት ተከትለው ገቡ፤ ኢየሱስም፣ “ዐይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤” ብለው መለሱለት። ከዚያም ኢየሱስ ዐይኖቻቸውን ዳስሶ፣ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። ዐይኖቻቸውም በሩ፤ ኢየሱስም፣ “ይህን ማንም እንዳያውቅ” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በአካባቢው ሁሉ ስለ ኢየሱስ አወሩ። ከዚያም ሲወጡ፣ በጋኔን የተያዘ ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑ ከወጣለት በኋላ ድዳው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም ተደንቀው፣ “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ምድር ታይቶ አያውቅም” አሉ። ፈሪሳውያን ግን፣ “አጋንንትን የሚያወጣው፣ በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ። ኢየሱስ በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ እንዲሁም ደዌንና ሕመምን ሁሉ እየፈወሰ በከተሞቹና በመንደሮቹ ዞረ። ሕዝቡም እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ ዐዘነላቸው። ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ ለምኑት።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች