ማቴዎስ 8:1-27

ማቴዎስ 8:1-27 NASV

ከተራራው በወረደ ጊዜም ብዙ ሕዝብ ተከተለው። እነሆ፤ አንድ ለምጻም ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበና ከፊቱ ተንበርክኮ እየሰገደለት፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው። ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ “ጌታ ሆይ፤ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቷል” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ ልፈውሰውን?” አለው። የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል፤ እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ በማእድ ይቀመጣሉ፤ መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም መቶ አለቃውን፣ “ሂድ! እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። ብላቴናውም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ። ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ጐራ ሲል የጴጥሮስ ዐማት በትኵሳት ታምማ ተኝታ አገኛት። እጇን ዳሰሳት፤ ትኵሳቱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው። በዚያ ምሽት በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። በዚህም ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤ “እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ።” ኢየሱስ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበው ባየ ጊዜ፣ ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው። በዚህ ጊዜ አንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህር ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጐጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ የለውም” ሲል መለሰለት። ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ አስቀድሜ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው። ኢየሱስ ግን፣ “ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ተከተለኝ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገብተው ሄዱ። ድንገት ኀይለኛ ማዕበል በባሕሩ ላይ ተነሥቶ ጀልባዋን እስኪሸፍን ድረስ አወካቸው፤ በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ቀሰቀሱትና፣ “ጌታ ሆይ፤ ጠፋን፤ አድነን!” አሉት። ኢየሱስም፣ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ ለምን ይህን ያህል ፈራችሁ?” አላቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ነፋሱንና ማዕበሉን ገሠጸ፤ ወዲያውም ጸጥታ ሰፈነ። ሰዎቹም፣ “ነፋስና ማዕበል እንኳ የሚታዘዙለት፣ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” እያሉ ተደነቁ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች