ማቴዎስ 7:21-29

ማቴዎስ 7:21-29 NASV

“በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል። በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዐመፀኞች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ። “እንግዲህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን ብልኅ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያን ቤት መታው፤ በዐለትም ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውለው ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያን ቤት መታው፤ ቤቱም ወደቀ፤ አወዳደቁም የከፋ ነበር።” ኢየሱስ ማስተማሩን በፈጸመ ጊዜ፣ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። ምክንያቱም እንደ አይሁድ ሃይማኖት መምህራናቸው ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበር ነው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች