ማቴዎስ 3:1-12

ማቴዎስ 3:1-12 NASV

በዚያ ወራት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። ስብከቱም፣ “ንስሓ ግቡ፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና” የሚል ነበር። በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረለት እርሱ ነው፤ “በምድረ በዳ፣ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጐዳናውንም አስተካክሉ’ እያለ የሚጮኽ ድምፅ።” የዮሐንስ ልብስ የግመል ጠጕር ሲሆን፣ ወገቡንም በጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሓ ማር ነበር። ከኢየሩሳሌም፣ ከመላው ይሁዳና በዮርዳኖስ ዙሪያ ካለው አገር ሁሉ ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይጐርፉ፣ ኀጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር። ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደሚያጠምቅበት ስፍራ ሲመጡ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የእፉኝት ልጆች! ከሚመጣው ቍጣ እንድታመልጡ ማን መከራችሁ? እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ‘አብርሃም አባት አለን’ በማለት አታስቡ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና። እነሆ፤ ምሣር የዛፎችን ሥር ሊቈርጥ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። “እኔ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ጫማውን መሸከም ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ፣ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እርሱም በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። መንሹ በእጁ ነው፤ ዐውድማውን ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውን በጐተራ ይከትታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}