ማቴዎስ 28:11-20

ማቴዎስ 28:11-20 NASV

ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ከጠባቂዎቹ ጥቂቶቹ ወደ ከተማ በመሄድ የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩላቸው። የካህናት አለቆችም ከሽማግሌዎች ጋራ ተሰብስበው ተማከሩ፤ ለወታደሮቹ በቂ ገንዘብ በመስጠት እንዲህ አሏቸው፤ “ ‘ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት’ በሉ፤ ይህ ወሬ በገዥው ዘንድ ቢሰማ እንኳ፣ እኛ እናስረዳዋለን፤ ምንም ክፉ ነገር እንዳይደርስባችሁ እናደርጋለን።” ወታደሮቹም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ ታዘዙት አደረጉ። ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዶች ዘንድ በሰፊው እንደ ተሠራጨ ነው። ከዚያም ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወዳለው ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ሄዱ። ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ ጥቂቶች ግን ተጠራጠሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህም አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች