በዚህ ጊዜ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፣ የኦሪት የሕግ መምህራንና የሕዝብ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ነበሩበት፣ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ነገር ግን ጴጥሮስ ከርቀት ሆኖ እስከ ሊቀ ካህናቱ ቅጥር ግቢ ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የሁኔታውን መጨረሻ ለማየት ከጠባቂዎቹ ጋራ ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ በሙሉ ኢየሱስን ለማስገደል የሐሰት ማስረጃ ይፈልጉ ነበር፤ ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም በቂ ማስረጃ አላገኙም። በኋላ ግን ሁለት ሰዎች ቀርበው፣ “ይህ ሰው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ውስጥ መልሼ ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል” በማለት ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ተነሥቶ በመቆም፣ “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ ንገረን” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀድዶ፣ “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሯል፤ ከዚህ ሌላ ምን ምስክርነት ያስፈልገናል? በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል መናገሩን እናንተው ራሳችሁ ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ ፊቱ ላይ እየተፉ በጡጫ መቱት፤ ሌሎቹም በጥፊ እየመቱት፣ “ክርስቶስ ሆይ፤ ማነው የመታህ? እስኪ ትንቢት ንገረን!” አሉት። ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተቀምጦ ሳለ አንዲት የቤት ሠራተኛ ወደ እርሱ ቀርባ፣ “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋራ ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን፣ “ምን እንደምትናገሪ እኔ አላውቅም” በማለት በሁላቸውም ፊት ካደ። ከግቢው መውጫ ወደ ሆነው በር ሲያመራ ሌላዋ ሠራተኛ ተመልክታው፣ በዚያ ለነበሩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋራ ነበር” አለች። እርሱም በመሐላ ቃል፣ “ሰውየውን አላውቀውም!” ሲል ዳግመኛ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ ቆመው የነበሩት ሰዎች ቀርበው ጴጥሮስን፣ “አነጋገርህ ስለሚያጋልጥህ፣ በርግጥ አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። እርሱም እየማለና እየተገዘተ፣ “እኔ ሰውየውን አላውቀውም!” አላቸው። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው፤ ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
ማቴዎስ 26 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 26
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 26:57-75
16 ቀናት
የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት እና ትንሣኤ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ ተገልፆል። ይህ የፋሲካ በዓል የሚነግረን ፣ እንዴት ኢየሱስ ክርስቶስ መራራ ፅዋን፣ መከራን እና ስቃይን በመስቀል ላይ ተቀብሎ ከሞት በመነሳቱ በትንሳኤው ለአለም ሁሉ የምስራች ዜናን አበሰረ ። ይህ አጭር ቪዲዮ ፣ የእያንዳንዱ ቀን ታሪክ በምሳሌ ይገልፃል።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች