ማቴዎስ 21:33-46

ማቴዎስ 21:33-46 NASV

“ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የዕርሻ ባለቤት የወይን ተክል ተከለ፤ በዙሪያውም ዐጥር ዐጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል ባሮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው። “ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች ባሮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም፣ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ። “ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “ታዲያ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት ሲመጣ፣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ ዕርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ኢየሱስም፣ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማእዘን ራስ ሆነ፤ ጌታ ይህን አድርጓል፤ ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን?” አላቸው። “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች፤ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ ደግሞ የሚወድቅበትን ማንኛውንም ሰው ይፈጨዋል።” የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እነርሱ የሚናገር መሆኑን ዐወቁ። ነገር ግን ይዘው ሊያስሩት ቢፈልጉም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ነቢይ አድርጎ ይመለከት ስለ ነበር ፈሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች